ኢትዮጰያና እስራኤል ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ ተስማሙ

129
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 ኢትዮጵያና እስራኤል ለዘመናት የዘለቀውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማሳደግ እንደሚፈልጉ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእስራኤሉን ፕሬዝዳንት ሬውቨን ሪቭሊን ትናንት ወደ ሱዳን ከማቅናታቸው በፊት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። አንድ የእስራኤል ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያን ሲጎበኝ የመጀመሪያው ሲሆን ፕሬዝዳንት ሬውቨን በአገሪቱ በነበራቸው የሶስት ቀናት ቆይታ የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ከውይይቱ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ እንደተናገሩት 'አገራቱ አሁን ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።" "መሪዎቹ አሁን ያለውን ግንኙነት በምን መልኩ ማሳደግ እንደሚችሉና ፤የሁለቱ አገራት ህዝቦች ከዚህ እድገት እንዴት መጠቀም እንደሚችሉም መክረዋል "በማለት ገልጸዋል። የግብርና ቴክኖሎጂ ማዘመን በተለይ በመስኖ እርሻ፣ የዝናብ እጥረት በሚኖርበት ወቅት ውኃን ለማቀብ እንዲሁም የአየር ጸባይ ለውጥንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አገራቸው በኢኮኖሚ ፣በማህበራዊና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸውላቸዋል። ፕሬዝዳንት ሬውቨን ከዚህ በተጨማሪ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር አሁን ያለውን ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ እንደምትፈልግም መናገራቸውን ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያና የእሰራኤል የንግድ ግንኙነት 100 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ሱሌማን ሁለቱ መሪዎች የንግድ ግንኙነቱን ለማሳደግና ቁጥራቸው የበዛ ባለሐብቶችን ለመሳብ እንደሚሰሩም መናገራቸውን አስታውቀዋል። ሁለቱ አገራቱ ከንግስት ሳባና ከንጉስ ሰሎሞን ዘመን አንስቶ ለረጅም  ዘመን የዘለቀ ወዳጅነት የመሰረቱ ሲሆን የዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን እኤአ በ 1992 በአዲስ መልክ አድሰውታል። ፕሬዝዳንት ሬውቨን የአገራቸውን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣የንግድ ማህበረሰብና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነችውን ታዋቂ እስራኤላዊት ድምፃዊ ኤስተር ራዳን አስከትለው ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም