በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተመረቱ የዋና አልባሳት ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ ቀረቡ

72

አዳማ ታህሳስ 21/2011 በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተመረቱ አምስት ሺህ ካርቶን የዋና አልባሳት ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ ቀረቡ።

የቻይናው አንቴክስ ግሩፕስ ጨርቃጨርቅ አምራች ኩባንያ ምርቱን ዛሬ በፓርኩ ውስጥ ያስተዋወቀበትን ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።

በፓርኩ ፋብሪካ በመትከል ቀዳሚ የሆነው ኩባንያ ያመረታቸው የዋና አልባሳት በአንድ ኮንቴይነር ተጭነው ወደ ውጭ ሲላኩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሸን ምክትል ኮሚሽነርና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኩባንያው ባለቤቶችና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የአንቴክስ ግሩፕስ ሊቀመንበር ሚስተር ኩዋን አንሁዋ በዚሁ ወቅት እንዳስታወቁት ኩባንያው ምርቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ ልኳል።

በስምምነቱ መሠረት ኩባንያው 100 ሺህ ዶላር ከሽያጩ ገቢ እንደሚያገኝ ገልጸው በቀጣይም ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በስፋት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነቱን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።

ኩባንያው በሙከራ ደረጃ በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 500 ዜጎች መቅጠሩን ያመለከቱት ሊቀመንበሩ፣በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ለ10 ሺህ ሰዎች ሥራ ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ኩባንያው መንግሥት ትኩረት ከሰጠው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከመሳተፍ ባሻገር፤ ምርቱን በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ በመላክ ፈር ቀዳጅ ሆኗል።

ኩባንያው በቀጥታ ፓርኩ ሲገባ አምስት ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ማስመዝገቡን ጠቁመው፣ የሥራውን አዋጪ በጥናት በማረጋገጥ ካፒታሉን ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር በማሳደግ ስምንት ሼዶችን ተረክቦ  ወደ ልማት መግባቱን አስታውቀዋል።

ኩባንያው ጨርቅ ሰፍቶ ከመላክ ባለፈ ጥሬ ጥጥን ወደ ጨርቅ በመቀየር የተቀናጀ የማኑፋክቸሪንግ ልማት ማካሄድ ሲጀምር ተጨማሪ ሥራ እንደሚያመቻችም ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው በአገሪቱ በመንግሥት እየተገነቡ ካሉ 11 ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል ስድስቱ ተጠናቀው ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ  ስራ ውስጥ ለመግባት እስካሁን አንቴክስ ግሩፕን ጨምሮ አራት የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፣ ቬንቸር የተሰኘ ኩባንያ ማሽነሪ ማስገባት ጀምሯል ብለዋል።

በአገሪቱ እየተካሄዱ ላሉት ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ግንባታ እስካሁን 780 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ይናገራሉ።

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ካገኙት መካከል ወጣት ሄለን ዘውዴ በሰጠችው አስተያየት ኩባንያው ቻይና ወስዶ ለስድስት ወራት አሰልጥኖ ሥራ ላይ እንዳሰማራት ትገልፃለች።

ምንም እንኳ የሚከፈላት ክፍያ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ሥራውን በፍቅር እየሰራች መሆኑን ተናግራለች።

በቀጣይ የደሞዝ ማስተካከያ እንዲደረግና የትራንስፖርት አገልግሎት ለሠራተኛው እንዲመቻች  ሄለን  ጠይቃለች።

ምክትል ኮሚሽነሩና ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ስለሚቀርበው ቅሬታ በሰጡት ምላሽ ሰራተኞች አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት ይዘው ስራ ውስጥ ስለማይገቡ ችግሩ እንደሚከሰት ይናገራሉ።

ነገር ግን ኩባንያዎች ካላቸው የማምረት አቅም ጋር ያገናዘበ ክፍያ፣የምግብና የቤት አገልግሎት እንዲያሟሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተመረቀው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም