27ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል ሲከበር በመንግስት የተያዙ አቅጣጫዎችን ሳይሸራረፉ በመተግበር ትርጉም ያለው ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

75
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 27ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል ሲከበር በመንግስት የተያዙ አቅጣጫዎችን ሳይሸራረፉ በመተግበር ትርጉም ያለው በዓል እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ድርሻ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለፀ። ጽህፈት ቤቱ 27ኛውን የግንቦት 20 የድል ቀን ከፌዴራል ተቋማት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በደማቅ ሁኔታ አክብሯል። በበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ወቅት የተገኙት የጽህፈት ቤቱ የይዘት የኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ እንደገለፁት፤ "በአሁኑ ወቅት እንደ አገር እየተመዘገቡ ያሉ ድሎች የግንቦት 20 ትሩፋቶች ናቸው" ብለዋል። በዓሉ ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ አዲሲቷን ኢትዮጰያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትና አገሪቷ ባለፉት ጊዜያት ከገባችበት ፈታኝና ውስብስብ ቀውስ ወጥታ በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሂደት ሌላኛውን ጉዞ የጀመረችበት ወቅት በመሆኑ ድርብ በዓል ያደርገዋል ብለዋል። አሁን የተገኘውን ሰላምና የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ እውን ለማድረግም በርካታ ዜጎች መስዋትነት የከፈሉበት በመሆኑ ድሉን በዘላቂነትና ጠንካራ መሰረት ለማቆም የተፈጠረውን ብሔራዊ አንድነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በመደማመጥና በመመካከር በፍቅር በመደመር የአገሪቷን ስም በበጎ ለማስጠራት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንዲተጋ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያሳሰቡት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም