በወላይታ ሶዶ ከተማ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

49

ሶዶ ታህሳስ 21/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ ዛሬ የተከሰተው የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡

የከተማው አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ያልሳ ጋጋ እንዳስታወቁት አደጋው ከሌሊቱ 11፡30 ላይ የደረሰው በተለምዶ ማሪያም ሰፈር የእንጨትና ብረታ ብረት ውጤቶችና ጋራዦች ባሉበት አካባቢ ነው።

አካባቢው ከእንጨትና ብረታ ብረት ምርቶች በተጨማሪ የመኪና መለዋወጫዎች ሽያጭን የሚያካትት ንግድ እንደሚከናወንበት ገልጸዋል።

በሥፍራው የተለያዩ ማሽኖችና ጣውላዎች እንዲሁም ተረፈ ምርቶች በመያዙ ንብረቱን ለማዳንና ቶሎ እሳቱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎት  እንደነበርም  ዋና ኢንስፔክተር ያልሳ አስረድተዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገው ርብርብ አደጋው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ተችሏል ብለዋል፡፡

የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኢንዶክትሪኔሽን ሥራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር የኔነሽ ዓለሙ በበኩላቸው ወቅቱ ከፍተኛ ኃይል ያለው ንፋስ ስለሚነፍስበት ጥንቃቄ  ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የገና በዓል እየቀረበ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በተለይ ከኤሌክትሪክና እሳት ጋር ግንኙነት ያላቸው ተግባራት ሲያከናወኑ ነዋሪዎች ጥንቃቄ  እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም