ከዲያስፖራው ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሰበሰበ

133

አዲስ አበባ ታህሳስ 21/2011 "አንድ ዶላር ከአንድ ማኪያቶ" በተሰኘው ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ ሂሳብ ቁጥር ከዲያስፖራው የሚሰበሰበው ገንዘብ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ደረሰ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት አንድ ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር የተከፈተ ሲሆን ከዕቅዱ በላይ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ዲያስፖራው ቃሉን አክብሮ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ገንዘቡ በዋናነት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተለይም ወሳኝ በሚባሉት የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦትና ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ለማዋል የታለመ ነው።

ለስራ ፈጠራ፣ ለግብርናና ቴክኖሎጂ ልማትም የሚውል ሲሆን ትረስት ፈንዱ የኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ በቀን አንድ ዶላር እና ከዚያም በላይ እንደየአቅሙ ለአገሩ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የተቋቋመ ነው።

በአዲሱ የአውሮፓውያን 2019 ዓመትም ዲያስፖራው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታመናል።

ከሶስት ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ የዲያስፖራ አባላት በተለያዩ የዓለም አገራት እንደሚኖሩ ይገመታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም