በሀገሪቱ የእቀባ እርሻን ለማስፋፋት ዝግጅት ተደረገ

61

አዳማ ታህሳስ 20/2011 የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንዲቻል የእቀባ እርሻን በሃገሪቱ ለማስፋፋት መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የእቀባ እርሻን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ ክልሎችና ወረዳዎች የማስተዋወቅና የማስፋት ስራን ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንዳሉት በሀገሪቱ ደጋግሞ በማረስ ላይ የተመሰረተው መደበኛ እርሻ  በደጋማ ቦታዎች ላይ የአፈር መሸርሸርን ፣ የለምነት መራቆትና መከላትን እያስከተለ ነው።

በቆላማ ቦታዎች ላይ ደግሞ ስር የሰደደ የአፈር እርጥበትና የአየር ንብረት መዛባት ችግሮችም እንዲሁ።

"በዚህም ምክንያት የሰብል ምርትና ምርታማነት ከማሽቆልቆሉም በላይ በሀገር ደረጃ የምግብ ዋስትናንና የሥነ-ምግብን አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል" ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከምርምር አካላት ጋር በመተባበር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባደረገው ጥናት የእቀባ እርሻ ለእነዚህ ተግዳራቶች አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ መረጋገጡን ዶክተር ካባ  አስታውቀዋል። 

የእቀባ እርሻን በግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቱ ውስጥ ለማካተትና ዘላቂነት ባለው መልኩ በየደረጃው አሰራሩን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የእቀባ እርሻን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የፖሊሲ ማዕቀፍና የአሰራር መመሪያ ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፍ የበቆሎና ስንዴ ማሻሻያ ምርምር ማዕከል  ተወካይ ዶክተር ክንዴ ተስፋዬ በበኩላቸው የእቀባ እርሻ የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች በቅንጅት በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል  ገልጸዋል፡፡

ይህም አፈርን፣ውሃን፣የአፈር ንጥረ ነገሮችንና የኃይል አቅርቦትን በመቆጠብ ምርትና ምርታማነትን እስከ 40 በመቶ በዘላቂነት ለማሳደግ ያስችላል።

የእቀባ እርሻ ደጋግሞ ማረስን መቀነስ፣በማሣ ላይ ቅሪተ ሰብልን ማስቀረት ፣ ሰብሎችን ማፋራረቅና ማሰባጠር መዝራት መሆኑን አብራርተዋል።

በሀገሪቱ ለእቀባ እርሻ ትግበራ በከፍተኛና በመካከለኛ ደረጃ ተስማሚ የሆነ ሶስት ሚሊዮን 800ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚገኝ በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብዮት መኮንን በሰጡት አስተያየት የእቀባ እርሻ በሙከራ ደረጃ በምስራቅ ጎጃም ዞን ከአንድ ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የአፈር ለምነቱ በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳ በመሆኑ ልማቱ በተጀመረ  ዓመት ለውጥ መገኘቱን ጠቁመው  በተለይ የበቆሎና የስንዴ ምርታማነትን በሄክታር 30 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

" የእቀባ እርሻ በክልሉ በአሲዳማነት የተጎዳውን አንድ ሚሊዮን 700 ሺህ ሄክታር መሬት ለመታደግ ወሳኝ ነው" ያሉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ከድር ናቸው፡፡

በተለይ አሲዳማ መሬቱ ካለበት መጠነ ሰፊ ችግር እንዲያገግምና ምርታማ እንዲሆን በመጪው የምርት ዘመን የትግበራ ምዕራፍ ውስጥ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአውደ ጥናቱ ከፌደራልና ከሁሉም ክልሎች እንዲሁም  ከምርምር ተቋማት የተወጣጡ የዘርፉ ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም