ህገ መንግስቱን ማን ይተርጉመው በሚል ጉዳይ ክርክር ተካሄደ

105

አዲስ አበባ ታህሳስ 20/2011 "ህገ መንግስቱን ማን ይተርጉመው" በሚል ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ክርክር ተካሄደ።

የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ባዘጋጀው በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ሰፊ ክርክር ተካሂዶባቸዋል።

የክርክሩ ዋነኛ ነጥቦች ያተኮሩት "ህገ መንግስቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መተርጎም አለበት" የሚል በአንድ ወገን ሲነሳ፤ በሌላ ወገን ደግሞ "ህገ መንግስት መተርጎም የፍርድ ቤት ጉዳይ ነው" የሚሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፖለቲካ የጋራ መግባቢያ ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም መጽደቁ ይታወሳል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንደሚያደራጅና ህገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን እንዳለው ያስቀምጣል።

በአንቀጽ 82 ላይም ጉባዔው 11 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ጉባኤውን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በሰብሳቢነትና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ደግሞ በምክትል ሰብሳቢ እንደሚመሩት ተመልክቷል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ በሙያ ብቃታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የህግ ባለሙያዎችና  ከፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሶስት አባላቶችን  እንደሚያካትት ተደንገጓል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት "የህገ መንግስት ተርጎሚ ይሁን አይሁን?" የሚለው ጉዳይ የዘርፉን ባለሙያዎች የመከራከሪያ ሃሳብ ከሆነ ሰነባብቷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአማራ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት የህግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ አለልኝ የኋላ እንደሚሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የፖለቲካ ሹመት ያላቸውና የየመጡበትን ክልል የሚወክሉ ናቸው።

ይህም በመሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ህገ መንግስቱን ነጻና ገለልተኛ ሆነው የመተርጎማቸው ጉዳይ 'ጥያቄ ውስጥ ይገባል' ይላሉ።

የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው ህገ መንግስት የሚተረጉሙት መደበኛ ፍርድ ቤቶችና ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን አውስተው፤ ይህ ተሞክሮ የኢትዮጵያን ተጫባጭ ሁኔታ አገናዝቦ ተግባራዊ ቢደረግ የሚል ሃሳብም አንስተዋል።

እንደ አቶ አለልኝ ገለፃ፤ በአገሪቷ ነጻና ገለልተኛ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት በማቋቋም ህገ መንግስቱን የመተርጎም ስራ ማከናወን ያስፈልጋል።

ይህም ህገ መንግስቱን እስከ ማሻሻል የሚሄድ ጉዳይ በመሆኑ "በተደጋጋሚነት የሚነሳውን የተርጓሜ ተገቢነት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል" ብለዋል።

የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባል አቶ ሚሊዮን አሰፋ በበኩላቸው ከህገ መንግስት አተረጓጎም ጽንሰ ሀሳብ አኳያ "ፍርድ ቤቶች ህገ መንግስትን ይተርጉሙ የሚለው ሃሳብ "ህጋዊ መሰረት የለውም"  ምክንያቱም የህገመንግስት ጉዳይ "የህገ መንግስት ጉዳይ የህግ ብቻ ጉዳይ አይደለም የፖለቲካና የፖሊሲ ዲሲሽን ጭምር ነው።” ብለዋል ።

ህገ መንግስቱ የህዝቡ ስለሆነ የሚተረጉመው አካል መኖር ስላለበት ጉዳዩ ከዚህ "አኳያ መታየት አለበት" ሲሉም አስረድተዋል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፖለቲካ የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመሆኑ "በገለልተኝነት የሚተረጉመው ማን ሊሆን እንደሚችል በጥልቀት ማየት ቢቻል" ሲሉም ሀሳብ ሰንዝረዋል።

እንደ አቶ ሚሊዮን ገለፃ፤ አሁን ካለው አገራዊ ለውጥ አንፃር ህገ መንግስቱን ማን ይተርጉመው? የሚለው ጉዳይ ሰፊ ጥናት ተደርጎበት መቅረብ አለበት።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እንደሚሉት፤ የህገ መንግስቱ ተርጓሚ አካል ቀደም ሲልም ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ነው።

የዚህ ውይይት መድረክም በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያሉ ሀሳቦችን በማንሳት በቀጣይ ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅመውን ነገር የማስቀመጥ የመጀመሪያ ተግባር እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የህገ መንግስት ተርጓሚ ተገቢነት ጥያቄ ሰፊና ጥልቅ ውይይት የሚፈልግ መሆኑን አመልከተው፤ በቀጣይም "ህዝቡ በየደረጃው እንዲወያይበት ይደረጋል" ብለዋል።

የህገ መንግስት ተርጓሚ ስልጣንና ተግባር ጉዳይን ማሻሻል ህገ መንግስትን ማሻሻልን የሚጠይቅ በመሆኑ፤ የህዝቡ ውይይት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዓለም አገሮች 86 በመቶ የሆኑት ህገ መንግስት የሚተረጉሙት በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ወይም በህገ መንግስት ፍርድ ቤት መሆኑንም ፕሬዝዳንቷ አስረድተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የህገ መንግስት ተርጓሚ አካል ላይ የሚነሱ የተለዩ ሃሳቦች ተፈጻሚ የሚሆኑት የህገ መንግስት ማሻሻያ ሲደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ የምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪነት "በህገ መንግስቱ በሰፈረው መሰረት ይቀጥላል" ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ህገ መንግስታዊ ፍልስፍና እንዲበለፅግ ማድረግ የህገ መንግስት ምሁራን የቤት ስራ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ከ1992 እስከ ጥቅምት 2010 ዓ.ም  ከቀረቡለት 3 ሺህ 724 ህገ መንግስታዊ አቤቱታዎች መካከል ውሳኔ  የተሰጣቸው 2 ሺህ 40 ብቻ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከነዚህ መካከል 65ቱ ብቻ የህገ መንግስት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው ተወስኖ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ተሰጥቶበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም