የህወሓት የወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

197

መቀሌ ታህሳስ 20/2011 ወጣቶች የትናንቱን ወርቃማ ታሪክ በመጠበቅ አዲስ ታሪክ ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ የተደራጀ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አሳሰቡ፡፡

የህወሓት የወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤ "ጉባኤያችን ፅናታችንና ድላችን ነው " በሚል መሪ ሀሳብ   ዛሬ    በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር ጉባኤውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት  የክልሉ ህዝብ በተለይም ወጣቶች በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት በየአካባቢያቸው ጠንክረው  ሊሰሩ ይገባል፡፡

" አሁንም እንደወትሮው የድርጅቱን  መስመር በመያዝና የህዝቡን  አንድነት በማጠናከር የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮችን ለመፍታትና ለውጥ ለማምጣት መታገል አለብን" ብለዋል፡፡

በክልሉ የመልካም አስተዳደር ፣የዴሞክራሲና የልማት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ውሳኔዎች ከጉባኤው እንደሚጠበቅም ዶክተር ደብረጽዮን ገልጸዋል፡፡፡

ህዝባችን በተለይም ወጣቱ  ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን በአጭር ጊዜ ከድህነት በማላቀቅ የህዝቡ ኑሮ የተሻለ እንዲሆን ሁሉም ወጣት በየአካባቢው ጠንክሮ መስራት አለበት ፤  በክልሉ የዴሞክራሲ የመልካም አስተዳደሮችና የልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት  የሚያግዙ ውሳኔዎች ከጉባኤው ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የህወሓት ወጣት ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሰናይ ከሃሰ በበኩሉ  የትናንት ታሪክ በሰላምና በልማት ለመድገም የክልሉ ወጣት ሊግ አባላት በሃገሪቱ  ከሚገኙ የሰላምና የልማት ኃይሎች ጋር በመሆን ትግላቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ  ብሄር ከብሄር ጋር ለማጋጨት የሚደረገው እንቅስቃሴ ጊዜ ሳይሰጠው ለማስቆም  ወጣቶች በጋራ መታገል አለብን ብሏል፡፡

በጉባኤው የወጣቶች ሊግ ባለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው ስራዎች ውስጥ የታዩ ጠንካራና ደካም ጎኖችን በመለየት እንደሚገመገም የገለጸችው ደግሞ  የሊጉ ምክትል ሊቀመንበር ወጣት ኤልሳ  ተስፋዬ ናት፡፡

በጉባኤው በወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩም ገልጻለች፡፡

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሙሉጌታ ተካ በበኩሉ "በወላጆቻችን የተረጋገጠው ሰላም ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል  ወጣቶች የተጣለብን ኃላፊነት ለመወጣት እንሰራለን "ብለዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤው ከ700 በላይ ወጣቶች፤ የእህትና አጋር ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም