በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የተገኘው የሰሊጥ በ760 ሺህ ኩንታል ቀንሷል

1392
OLYMPUS DIGITAL CAMERA

ሁመራ ታህሳስ 20/2011 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በመኸር ወቅት የተገኘው የሰሊጥ ምርት ከእቅዱ በ760 ሺህ  ኩንታል መቀነሱን የዞኑ የግብናና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ በ2010/2011 ምርት ዘመን መኽር ወቅት አንድ ሚሊዮን 40 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት መገኘቱን ተገልጻል ።

በመምሪያው የስነ- አዝርት አስተባባሪ አቶ ተክለማርያም ነጋ ለኢዜአ እንደገለጹት በምርት ወቅቱ ታርሶ በዘር ከተሸፈነው  286 ሺህ 827 ሄክታር መሬት አንድ ሚሊዮን 800ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ለማግኘት ታቅዶ ነበር ።

የተገኘው ምርት ከእቅዱ በ760 ሺህ ኩንታል እንዲሁም ካለፈው ተመሳሳይ ምርት ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ400 ሺህ ኩንታል መቀነሱን ጠቁመዋል።

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የፀረ-ሰብል ተባይ ክስተት ማጋጠሙ ፣ ዘር በመስመር አለመዝራትና የምርት ማሳደጊያ ግብአት በአግባቡ አለመጠቀም ለምርት መቀነሱ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በቀጣዩ ምርት ወቅት እነዚህን ክፍተቶች በማረም የተሻለ ምርት መጠን ለማግኘት አቅጣጫ ተይዟል ።

በዞኑ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ  ባለሀብቶች መካከል አቶ ተመስገን መለስ በምርት ወቅቱ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ ተጠቅመው በመዝራታቸው በሄክታር ያገኙት የነበረው  ሶስት ኩንታል ሰሊጥ ወደ አምስት ማደጉን ተናግረዋል ።

በምርት ወቅቱ አርሰው በበሰሊጥ ዘር ከሸፈኑት 100 ሄክታር መሬት 500 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አመልክተው ያልተጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ መጠነኛ ጉዳት ባያስከትልባቸው የተሻለ ምርት ማግኘት ይችሉ እንደነበር ገልጸዋል።

ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ባለመጠቀማቸው ዝቅተኛ ምርት ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ በወረዳው በተመሳሳይ ልማት የተሰማሩ ባለሀብት አቶ ደስታ ተክላይ ናቸው፡፡

በሰሊጥ ዘር ከሸፈኑት 50 ሄክታር መሬት ከአንድ መቶ ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የቃፍታ ሁመራ ወረዳ አርሶ አደር ብረሃነ ገብረ ኪዳን በሰጡት አስተያየት ምርጥ ዘር ተጠቀመው ካለሙት  ሁለት ሄክታር መሬት 14 ኩንታል  እንዳገኙ ጠቅሰው ባንጻሩ ነባሩን ዘር ተጠቅመው ካለሙት ሁለት ሄክታር ማሳ የሰበሰቡት ምርት አራት ኩንታል መሆኑን ተናግረዋል፡፡