በቆጠራው የአካል ጉዳተኞች ትክክለኛ ቁጥር መረጃ እንዲሰበሰብ እየተሰራ ነው

120

አዳማ ታህሳስ 20/2011 ዘንድሮ በሚካሔደው አራተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የአካል ጉዳተኞችን ትክክለኛ ቁጥር የሚያመላክት መረጃ እንዲሰበሰብ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ ።

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንዳሉት በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው ሶስተኛው ዙር የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ይፋ የተደረገው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በርካታ ክፍተቶች ነበሩ።

" በወቅቱ ይፋ የተደረገው የቆጠራ ውጤት ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር 1 ነጥብ 1 በመቶ ብቻ ነው የሚልና የተሳሳተ መረጃ ነበር" ብለዋል ።

በዚያን ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር 15 በመቶ ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 17 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን የዓለም ባንክና የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ ይፋ አድርገው እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል ።

ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በወቅቱ ያወጣው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ዝቅተኛ መሆን አገልገሎት ሰጪዎች አናሳ በጀት እንዲይዙ በማድረጉ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዳይሆኑ ማድረጉን አመልክተዋል።

ለአካል ጉዳተኞች የትምህርት ፣ በጤናና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ሲጠየቅ በዓመት ከሶስት ያልበለጡ የአካል ጉዳተኞች ይመጣሉ ብለን ከፍተኛ በጀት አንመድበም የሚል የተሳሳተ መልስ  እንዲሰጣቸው ያደረገው የቆጠራው  ውጤት መሆኑን ተናግረዋል ።

" ችግሩ የግንዛቤ ማነስና ቆጠራው በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ ስለነበር ነው" ያሉት አቶ አባይነህ ዘንድሮ ተመሳሳይ ክፍተት እንዳይፈጠር ከኤጀንሲው ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የህዝብ ቆጠራ ዳይሬክተር አቶ አባተ ሲደልል በበኩላቸው በሶስተኛው ዙር የታዩትን ክፍተቶች በመሙላት በቆጠራው ትክክለኛውን የአካል ጉዳተኞች ቁጥር የሚገልፅ መረጃ ለመሰብሰብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

ለቆጠራው ከተዘጋጁ ከ80 በላይ መጠይቆች መካከል አካል ጉዳተኞች የሚመለከቱ ብዛት ያላቸው መጠይቆች መካተታቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተሰማ ሰብስቤ እንዳሉት ትክክለኛ መረጃ ለፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነት ወሳኝ በመሆኑ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በትክክል መያዝ አለበት ።

"በሶስተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የነበረው ትልቁ ችግር የአካል  ጉዳተኞች ተሳትፎ ደካማ ስለነበር ነው" ያሉት  አቶ ተሰማ ዘንደሮ ግን በሁሉም ዘርፎች ተሳትፏቸውን በማጠናከር ትክክለኛ መረጃ እንዲሰበሰብ የድርሻቸው እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በሶስተኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ወቅት የታዩ ክህተቶችን ለመሙላት ዛሬ በአዳማ ከተማ የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ፣ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት የሁለት ቀናት የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና ተጀምሯል ።

ስልጠናው በህዝብ ቆጠራ አስፈላጊነት ፣በአራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ቅድመ ዝግጅትና በአካል ጉዳተኞች አካታችነት ላይ ያተኮረ መሆኑን  በኤጀንሲው የህዝብ ቆጠራ ከፍተኛ በለሙያ አቶ አሰፋ ነገራ ናቸው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም