በድብቅ በተሽከርካሪ ተጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ የጦር መሣሪያ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በድብቅ በተሽከርካሪ ተጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ የጦር መሣሪያ ተያዘ
52
አዲስ አበባ ታህሳስ 20/2011 የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በድብቅ በተሽከርካሪ ተጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኤ 62632 አ.አ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ተጭኖ በድብቆ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ ኤኮል ፒ 29 የተባሉ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ኮሚሽኑ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ ሁለቱ ተቋማት ታህሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በጋራ በመሆን ክትትል አድርገዋል።
በመሆኑም ወደ አዲስ አበባ ተጭኖ ሊገባ የነበረ ብዛቱ 180 የሆነ ሽጉጥ ለመያዝ ተችሏል።
ሽጉጦቹን ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር መዋሉን የገለጸው ኮሚሽኑ በሕገ- ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ ተሳትፎ የነበራቸውን አሽከርካሪውና ረዳቱ ተይዘው ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም ይሄው በጎ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።
ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸንና ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በመቀናጀት ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን ያስታወሰው የኮሚሽኑ መግለጫ ወደ ፊትም የክትትል ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።