መገናኛ ብዙሀን በህዝቦች መካከል መጠራጠር እንዲነግስ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ሲአን ጠየቀ

143

ሀዋሳ ታህሳስ 20/2011 መገናኛ ብዙሀን ሚዛናዊነቱን ባልጠበቀ ዘገባ በህዝቦች መካከል መጠራጠር እንዲነግስ ከማድረግ እንዲቆጠቡ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ/ሲአን/ ጠየቀ፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ መግለጫ ለዘመናት ተዋደውና ተቀላቅለው በጋራ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ ሌት ተቀን የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሀን እንዳሉ አመልክተዋል፡፡

እነዚህ  ማህበራዊ ድረገጾችና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚንቀሰቃሱ መገናኛ ብዙሀን ለህዝቦች አንድነት መስራት አለባቸው፡፡

ሰሞኑን በሀዋሳ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አካባቢ ተከስቶ የነበረውን ሁከት ሳያጣሩ በመገናኛ ብዙሀን በመልቀቅ ህዝቦች እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ እያደረጉ ነው፡፡

"ባለፉት ስምንት ወራት የመጣው ለውጥ ወደ ውጭ ተሰደው የነበሩ ምሁራን ፣ ጸሀፊዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሀን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል" ብለዋል፡፡

የንቅናቄው ሊቀመንበር እንዳሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ  ጸረ ለውጥ ኃይሎች በተለያየ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

አንዳንድ የለውጡ ተጠቃሚ በመሆን ወደ ሀገር የገቡ መገናኛ ብዙሀንና ታሪካዊውን ለውጥ በስጋት የሚያዩ አካላት ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦችን ለመለያየት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡

"ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ በጭቆና ላይ በነበረበት ጊዜ ያግዙ የነበሩ በውጪ ሀገር ሲንቀሳቀሱ የቆዩና አሁን ግን በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በዋናነት ኢሳት በሀዋሳ በቅርቡ የተከሰተውን ችግር ሳይጠና በአንድ ህብረተሰብ ክፍል ላይ በማነጣጠር ያሳራጨው ዘገባ ትክክል አይደለም" ብለዋል፡፡

የሲአን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሜሳ በበኩላቸው “አንዳንድ የመንግስት ኃላፊዎች ህገመንግስታዊ የብሄር መብትን የተጻረረ አዝማሚያ ያለው ንግግር በየመድረኩ በመንዛት በህዝቦች መካከል ሁከትና ሽብር እንዲፈጠር የሚያደርጉትን ሙከራ እናወግዛለን” ብለዋል፡፡

የሲዳማ ወጣቶች እንደ ሁሉም የሀገሪቱ  ወጣቶች የህዝቦች ስጋት ማስወገጃ ሰላማዊ ኃይል እንጂ የስጋት አካል እንዳልሆኑ ገልጸው  ከዚህ በተጻራሪ መልኩ የወጣቱን ስም ለማጥፋት የለውጥ አደናቃፊ አስመስለው የሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሀንና አንዳንድ የመንግስት ሹማምንቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡

ሲዳማ  ለዘመናት ሲጠይቀው የነበረው በክልል የመደራጀት ህገ መንግስታዊ መብት የመጨረሻ ምዕራፍ የሆነው ህዝበ ውሳኔ ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድና ሂደቱም የደረሰበት ደረጃ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግም አመልክተዋል፡፡

አንዳንድ ጸረ ለውጥ የሆኑና የሲዳማን ባህላዊ አልባሳት ያደረጉ በከፊል ሲዳሚኛ የሚናገሩ አካላት በሲዳማ ስም እየተንቀሳቀሱ ህዝብን ለማራራቅ እንደሚጥሩ ጠቅሰው ይህንን ለማጋለጥ ከህዝቡ ጋር አንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡

ሲአን በወቅታዊ  እንዲሁም በሀዋሳ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ዙሪያ ከነዋሪው ህዝብ ጋር ከመጪው ሳምንት ጀምሮ እንደሚወያይ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም