በአፋርና ኢሳ ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

56

ሰመራ ታህሳስ 19/2011 በአፋርና ኢሳ ማህበረሰብ መካከል  የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ አውሲ እና ገቢ  ዞኖች ውስጥ የሚገኙት ሁሉቱ ወንድማማች  ማህበረሰቦች በሰላም በመኖር ዘመናት ያስቆጠረ አብሮነት ያላቸው ናቸው፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ መሃመድ እንደገለጹት አፋርና ኢሳ ማህበረሰብ ለረጅም ዘመናት በግጦሽ ይገባኛልና ተያያዥ ጉዳዮች  ባለመግባባት ይጋጩ ነበር፡፡

ሁለቱ  ወንድማማቾች  በጋራ ተስማምተው መኖር የሚያስችል ስምምነት ከስድስት ዓመታት በፊት በአፋርና በሱማሌ ክልሎች መካከል ተፈርሞ ችግሩ እልባት ማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ሶስት የኢሳ ማህበረሰብ ቀበሌዎች የአፋር ክልላዊ መንግሰት ህጋዊ እውቅና ሰጥቷቸው ያለምን ችግር  ከወንድሞቻቸው ጋር  ተከባብረው በሰላም እየኖሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

አቶ አህመድ እንዳሉት በቅርቡ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በክልሉም ለማስቀጠል እንቅስቃሴ በሚደርግበት ወቅት  በአንዱ ቀበሌ ህጋዊ ባልሆነ አግባብ  የሁለቱን ወንድማማች ማህበረሰብ አብሮነት ለማሻከር ግጭት ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡

የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መስመርን   ለማስተጓጎልም እንዲሁ፡፡

ይህንን ህገወጥ እንቅስቃሴ  በመቆጣጠር በአካባቢው  የህግ የበላይነትን ለማስከበር ግዳጅ ላይ በነበሩ የጸጥታ አካላት  ላይም ጥቃት በመፈጽም በሁለቱም ወገን የሰዎች ህይወት መጥፋቱን የገለጹት አቶ አህመድ በህብረተሰቡና በመንግሰት ርብርብ አሁን አካባቢው መረጋጋቱን አስታውቀዋል፡፡

አካባቢው የኮንትሮባንዲስቶች  እንቅስቃሴ የሚስተዋልባትና ይህን የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚፈልጉ ግለሰቦች ችግሩ እንዲፈጠር ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ችግር ፈጣሪዎችን ለይቶ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግብብ የክልሉ ጸጥታ ኃይል  ከፌዴራል ፖሊስና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡

የተፈጠረው ችግር ማህበረሰቡን እንደማይወክል ያስታወቁት አቶ አህመድ  የሁለቱ ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ ወንድማማችና አብሮነት ለማስቀጠል ችግሮች በውይይትና ምክክር  እንዲፈቱ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ቢሮው እያዘጋጀ ባለው የ100 ቀናት እቅድ  ውስጥ ለማከናወን ቅድሚያ ከሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ የማህበረሰቡን  የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

አዋሳኝ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች ለመፍታት ክልሉ ከአጎራባች ክልሎች ጋር  ተቀራርቦ  የህዝብ ለህዘብ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክርም  የቢሮው ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም