የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሁንም ከኦዲት ግኝት ችግር መውጣት አልቻለም--የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

76
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2010 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሁንም ከሂሳብ ኦዲት ችግር መውጣት አለመቻሉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናገረ። ዩኒቨርሲቲው "ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ ለአገር ሲያበረክት እንዴት የራሱን የሂሳብ አሰራር ማዘመኛ ዘዴ መፈለግ ቸገረው?" ሲልም ምክር ቤቱ ጠይቋል። የምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዩኒቨርሲቲውን የ2008 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ማስተካከያ ሪፖርት ዛሬ መርምሯል። ዩኒቨርሲቲው መንግስት ያወጣውን የግዥ መመሪያ ተከትሎ ግዥ አልፈጸመም፤ የሚሰሩ የፕሮጀክት ሂሳቦች ለተባለው ዓላማ መዋላቸውን የሚገልጽ ማስረጃ አላቀረበም፤ ከህግ ውጪ ክፍያዎችን ይፈጽማል ተብሏል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ተሰብሳቢ ሂሳቦችን አለመሰብሰብና ሌሎች ችግሮች መኖራቸውን የዋና ኦዲተር ግኝቱ ያስረዳል። ዩኒቨርስቲው ከ679 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብሳቢ ሂሳብ መሰብሰቡን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለማቅረቡ እንዲሁም ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ብር ከህግ ውጪ መክፈሉን የሂሳብ ኦዲት ግኝቱ አረጋግጧል። በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን ግንባታዎች ስራ ተቋራጮች ግንባታው መጠናቀቅ ከነበረበት ቀን ሲያራዝሙ መክፈል የነበረባቸውን ከ19 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መሰብሰብ አልቻለም ተብሏል። በኦዲት ግኝቱ መሰረት የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እራሱ ባዘጋጀው የክፍያ ስርዓት ብቻ ለግንባታ ዘርፍ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ፈጽሟል። ዩኒቨርሲቲው እነዚህና ሌሎች በሚሊዮንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከመመሪያና ህግ ውጪ የተከፈሉ፤ ግዥ የተፈጸመባቸው፤ ያልተሰበሰቡ  ሂሳቦች ተብለው በኦዲት ግኝቱ ተዘርዝረዋል። የተጠቀሱት የሂሳብ ኦዲት ግኝቶች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችና ዩኒቨርሲቲው መመሪያና ህግን ተከትሎ ለምን መስራት አቃተው? እንዲሁም ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝቶችን ለምን ማስተካከል አልቻለም? ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሃላፊዎችን ጠይቀዋል። የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ማቲያስ እንሰርሙ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝት ከአሰራር ስህተት የመነጩ ናቸው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህም ተቋሙ ያልዘመነ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት መጠቀሙ መሆኑን ጨምረው በመግለጽ በግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ እየወሰዱ መሆኑንም አስረድተዋል። ሌሎች የሚመለከታቸው የተቋሙ ሃላፊዎችም የኦዲት ግኝቶች እየተስተካከሉ መሆኑንና የሚከፈሉ የጥቅማጥቅም ክፍያዎችንና ሌሎችን የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ፈቅዶላቸው ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል። ሃላፊዎች ይህን ይበሉ እንጂ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የኦዲት ግኝቱን ዋና ኦዲተር ባስቀመጠው የኦዲት ማስተካከያ መሰረት ምንም ዓይነት የማስተካከያ እርምጃ አለመወሰዱን አረጋግጠናል ብለዋል። የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ማንኛውንም ጥቅማጥቅም የሚመለከቱ ክፍያዎችን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እውቅና ውጪ ማንም ሊፈቅድ እንደማይችል በማስገንዘብ የቦርዱ ውሳኔ ነገም የኦዲት ግኝት ሆኖ ይመጣል የሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። የዩኒቨርስቲው ሃላፊዎች እርምጃ ሊወስዱ ያልቻሉበትን ምክንያት በግልጽ ካላስቀመጡ ችግሩን የፈጠሩ ሃላፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። የዩኒቨርስቲው የ2009 በጀት ዓመት ኦዲት ግኝት ከ2008 የባሰ መሆኑን በመግለጽ እየተጠናቀቀ ያለው የ2010 በጀት አመት የተነሱ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ጌሌሶ ዩኒቨርሲቲው መንግስት የሚያወጣቸውን መመሪያዎችና ደንቦች አክብሮ ከመስራት አኳያ ትልቅ ችግር አለበት ብለዋል። በመሆኑም የሚወጡ መመሪያዎችንና አሰራሮችን ተከትሎ መስራት እንዳለበትና አሰራሩን ካላሻሻለ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ነው ያሳሰቡት። ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በ2007 በጀት ዓመት የተገኙ የኦዲት ውጤቶችንም  የእርምት እርምጃ  አለመውሰዱን ምክር ቤቱ አንስቷል። በተመሳሳይ በ2008 መጀት ዓመትም የታዩ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል መሻሻል የማይታይበትና በፋይናንስ ህግና ደንብ በመስራት በኩል ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእውቀት መፍለቂያ ሆኖ ሳለ በየዓመቱ እየጨመረ የሚሄድ ከፍተኛ የኦዲት ግኝት ችግር ያለበት ከመሆኑ ባሻገር በግኝቱ ላይ የእርምት እርምጃም ሲወስድ አይታይም ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም