በጋምቤላ በግብርና ለመሰማራት ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች ወደ ስራ የገቡት ከግማሽ በታች ናቸው

1054

ጋምቤላ ታህሳስ 19/2011 በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት  ፈቃድ ከወሰዱ ከፍተኛና መካከለኛ ባለሀብቶች መካከል ወደ ስራ የገቡት ከግማሽ በታች መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ፡፡

በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ስራዎች ዙሪያ ያተኮር የምክክር መድረክ  በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በምክክር መድረኩ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በግብርና ኢንቨስትመንት ከ700 በላይ ከፍተኛና መካከለኛ ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ወደ ስራ የገቡት ከግማሽ በታች ናቸው።

ለእነዚሁ ባለሃበቶች ከተላለፈው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬትም ወደ ልማት የገባው ከ20 እስክ 30 በመቶ ብቻ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ዝቅተኛ አፈፃፀም ሊታይ የቻለው የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የባለሀብቱ ተነሳሽነት ማነስ፣ ባለሀብቶች የባንክ ብድር ከወሰዱ በኋላ ጥለው መጥፋት ርዕሰ መስተዳደሩ ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል ይገኙበታል።

“በዘርፉ የታዩ ማነቆዎችን በማስተካከል ለግብርና ኢንቨስትመንቱ ውጤታማነት የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል “ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉን ኢንቨስትመንተ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ተጠናቆ ውሳኔ ተሰጥቶበት የማስተካከያ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀውም  ከባለድርሻ አካላት እየተከናወኑ ለሚገኙ ስራዎች ተጨማሪ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ  መሆኑን አቶ ኡሞድ አስታውቀዋል፡፡ 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በበኩላቸው ” በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆችን ለመፍታት ቢሮው የተለያዩ ባለርሻ አካላትን አካቶ እየሰራ ነው” ብለዋል።

በተለይም በባለሀብቶች መካከል የሚታዩ የካርታ መደራረብና የወሰን ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በእስካሁኑ ሂደት የ489 ባለሀብቶች ችግር መፈታቱን ገልጸዋል። 

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ  ባለሃብቶችን ፣  የክልል፣ የዞንና የወረዳ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።