በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦች ተወገዱ

856

ሽሬ ታህሳስ 19/2011 የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦች እንደወገዱ መደረጉን የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የከተማዋ ጤና ጽህፈት ቤት ከታህሳስ 17 ቀን 2011 ዓ ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት ድንገተኛ ቁጥጥር ማካሄዱን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መኮነን ገብረሚካኤል ዛሬ ለኢዜአ ገልፀዋል።

”በ20 የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች በተደረገው ድንገተኛ ቁጥጥር ከ5 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጦች ተገኝተዋል” ብለዋል።

ከ53 ሺህ ብር በላይ ዋጋ የነበራቸው እነዚህ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው በደረቅና በፈሳሽ መልክ የተዘጋጁ ምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጦች ተሰብስበው እንዲወገዱ ተደርጓል።

ህብረተሰቡ የታሸጉ ምግቦች ከመግዛቱ በፊት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያላለፈ ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሸቀጣሸቀጥ ንግድ የተሰማሩ አካላትም ሥራቸውን በኃላፊነትና በታማኝነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግብ ነክ ሸቀጦች ይዘው የተገኙት ነጋዴዎችም የምክርና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

የህክምና ባለሙያው ዶክተር ማትያስ አስመላሽ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦች ለተለያዩ የጤና ችግር እንደሚዳርጉ ገልፀዋል።

በተለይ ህፃናትን በቀላሉ ሰለሚጎዱ ወላጆች የሚገዟቸው የታሸጉ ምግቦች የመጠቀሚያ ጊዜ ያላለፈባቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸውማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የተዘጋጁ የፍራፍሬ ውጤቶች ይዘው የተገኙ አቶ ገንዘቡ በላይ እንዳሉት ”ከጅምላ ነጋዴዎች ስንገዛ አይነቱን እንጂ የመጠቀሚያ ጊዜ አናይም” ብለዋል፡፡

ይህን የግንዛቤ ችግር በማስተካከል በቀጣይ  የመጠቀሚያ ጊዜውን ጭምር በማስተዋል እንደሚገዙ ገልፀዋል፡፡

“በህብረተሰቡ የሚደረሰው የጤና ችግር የኛም ችግር በመሆኑ ለምንገዛውና ለምንሸጠው ምግብ ነክ ይሁን ሌላው ሸቀጥ የመጠቀሚያ ጊዜው በሚገባ በማስተዋል በኃላፊነት መንፈስ እንሰራለን” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ምፅላል ሓለፎም ናቸው።

”የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ማንኛውም ሸቀጣሸቀጥ በሌላ አካል ተገደን ሳይሆን ራሳችን ማስወገድ ይጠበቅብናል” ሲል አስተያየቱን የሰጠው ሌላው በንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት አለማየሁ ተስፋይ ነው።