''በአገሪቱ በግጭቶች የተፈናቀሉትን ዜጎች በዘላቂነት ለማቋቋም የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል''-ኮሚሽነር ምትኩ

125

አዳማ ታህሳስ 19/2011 በአገሪቱ በግጭቶች የተፈናቀሉትን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ  ዜጎች በዘላቂነት ለማቋቋም የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አመለከተ።

ግጭቶች በዘላቂነት በሚፈቱበት ሂደት ላይ ያተኮረ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ የፌዴራልና ክልል የዘርፉ ተቋማት የተሳፉበት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በየአካባቢው በተቀሰቀሱ ግጭቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በጋራ መሥራት ያስፈልጋል።

ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ጠንሳሽና አባባሽ አካላትን መለየትና እርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የዜጎች ተሳትፎና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ፣የሃይማኖት ተቋማት፣ መሪዎችና የሕዝብ አደረጃጀቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም ችግሩን ለመፍታት ድርሻቸውን እንዲወጡም ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ የዕለት እርዳታን ከማድረስ ጀምሮ ተፈናቃዮቹን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች አርሶና አርብቶ አደሩ ከምርት ተግባሩ በመነጠሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የሚያስገቡ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ያወሱት ኮሚሽነሩ፣እናቶች፣ ህፃናት፣አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ለእንግልትና ጉዳት ከመዳረጋቸውም ባሻገር፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መነጠላቸውን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በጌዲኦና በጉጂ ዞኖች ፀጥታ የማስፈንና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ ለውጥ እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን አለመግባባትና ግጭቶችን ለመፍታት በክልሎቹና በፌዴራል መንግሥታት እየተደረገ ባለው አንቅስቃሴ መረጋጋት እየተመለሰ ነው ብለዋል።

በኦሮሚያና ቤንሻንግል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት የሁለቱ ክልል ርዕሳነ መስተዳድር በትብብር እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት አመራርና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሰል ሙሐመድ ናቸው።

ከክልሉ ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙት ዜጎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከክልሉ መንግሥት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትንም ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ በሁለቱ መንግሥታት ደረጃ የጋራ ዕቅድ አውጥተው በመሥራት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የሚገኙ ከ60ሺህ በላይ ተፈናቃዮች የዕለት ዕርዳታ እንዲያገኙ ክልሉ ከፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ዱቄትና አልሚ የእናቶችና የህፃናት ምግብ እያቀረበ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በግጭትና በድርቅ  ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እየተረዱ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም