ኦዴፓ ከኦነግ በስተቀር "በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር በሰላም እየሰራሁ ነው" አለ

144

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2011የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከኦነግ በስተቀር በክልሉ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ፓርቲው በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በምን መልኩ እየሰራ እንደሆነ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኦዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የህዝብ አስተያየትና የህዝብ ግንኙነት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ታዬ ዳንዳአ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ከአንድ ፓርቲ በቀር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኦዴፓ የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው ከውጭ የመጡና በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተግባቡባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እየሰራ ነው።

የህግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለውጥ ለማስቀጠል በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የርዕዮት ዓለም ልዩነት ቢኖራቸውም አንድ በሚያደርጋቸው ጉዳይ ላይ ተግባብተው እየሰሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

ኦዴፓ ከፓርቲዎች ጋር በቅንጅትና በመዋሃድ እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ታዬ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የህዝብ አንድነት የሚጻረር ፖሊሲ ሊኖራቸው እንደማይገባም አንስተዋል።

ፓርቲው የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አንድነትና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ለማድረግ የፖለቲካ መርሃ ግብሩን እየፈተሸ መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ታዬ ኦነግ ወደ ስምምነት አለመምጣቱን አመልክተው፤ በየአካባቢው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና እየተወሰደ ያለውን እርምጃ፣ በቀጣይ አቅጣጫዎች ህዝቡ ማወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በኦሮሚያ ክልል 15 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚንቀሳቀሱ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም