ሚኒስቴሩ የህዳሴ ግድብ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃ በወቅቱ ማድረስ አለበት ተባለ

121

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2011 የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በሚመለከት ትክክለኛ መረጃ በወቅቱ ማድረስ እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ የሚኒስቴሩን የሶስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ እንደተናገሩት የግድቡ ግንባታ ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት የሚወጡ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው።

ይህም ህዝቡ በሚያደርገው ተሳትፎ ላይ ጥርጣሬ እንደሚያሳድርና ስለ ግድቡ ግልጽ መረጃ ወቅቱን ጠብቆ ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባ መክረዋል።

በዚህም የግንባታውን ደረጃም ሆነ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በሚመለከት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን በመውሰድ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው አሳስበዋል።

በተመሳሳይም ከኃይል አቅርቦት ሽፋን ጋር ተያይዞ የሚወጡ መረጃዎችም እንዲሁ ወጥነት ይጎድላቸዋል ነው ያሉት።

የኃይል አቅርቦት ሽፋን በተጨባጭ ያለበት ሁኔታና የትኞቹ አካባቢዎች ላይ በስፋት መሰራት እንዳለበት የተሟላ መረጃ በማድረስ በኩል ክፍተት እንዳለ በመጠቆም።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በቂና አሳማኝ ምክንያት ሳይኖራቸው የሚጓተቱ ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እርምጃ መውሰድ መጀመር አለበት ሲሉ አመላክተዋል።

ለአብነትም የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ መከናወን ያለባቸው አካባቢዎች የተለዩ ቢሆንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ስራው መከናወን አልቻለም የሚል ሃሳብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

በተጨማሪም የልማት ተነሺ አርሶአደሮች በየወቅቱ የሚያነሱት የካሳ ክፍያ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ የስራ ዕድል ጥያቄና የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት ከተሰራ በኋላ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በወቅቱ መከታተል ላይ ክፍተቶች መስተዋላቸውን አንስተዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በሰጡት ምላሽ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት በዓመቱ መጀመሪያ ላይ በመጀመሪያው ኮንትራክተር ያልተሰሩና የግድቡ ማነቆ ችግር ሆነው የቆዩ ጉዳዮችን በመለየት ሊሰሩ ወደሚችሉና አቅም ወዳላቸው አለም ዓቀፍ ኩባንያዎች የተዘዋወሩ ስራዎች አሉ ብለዋል።

ስለዚህ እነዚህና ሌሎች ስራዎች ምን እንደሚመስሉና በምን ሂደት ላይ እንዳሉ፣ ግድቡም አሁን በትክክል ያለበትን ደረጃ በሚመለከት ለህብረተሰቡ በውይይትና በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የማስረዳት ስራ ይከናወናል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ አሁን ባለው መረጃ መሰረት የግድቡ ግንባታ 65 በመቶ የደረሰ ሲሆን በግማሽ ዓመት 70 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

በዕቅዱ መሰረትም 70 በመቶው በተያዘው ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን በአራት ዓመት የግድቡን ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ አክለዋል።

የፕሮጀክቶች መዘግየትን በሚመለከትም የተለያዩ መንስኤዎች እንዳሉ በመጠቆም የአፈጻጸም ችግር፣ የኮንትራክተሮች አቅም ማነስ፣ የክትትልና ድጋፍ ድክመቶችና የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም