የባህልና ጥበባት ምክር ቤት የመቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ለውይይት ቀረበ

68

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2011 በባህልና ጥበባት ዘርፍ የተቀናጀ አሰራርና መንግስት በተደራጀ መልኩ ድጋፍ እንዲሰጥ ለማስቻል አዲስ ምክር ቤት ለማቋቋም ረቂቅ ደንብ ለውይይት ቀረበ።

ይህንኑ የ"ባህልና ጥበባት ምክር ቤት የማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብን" ለማዳበር የሚያስችል ሀሳብ ለማሰባሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

ረቂቅ ደንቡን የማዘጋጀት ስራ በ2003 ዓ.ም ቢጀመርም አደረጃጀቱን ለመወሰን ጊዜ መውሰዱ ለመዘግየቱ በምክንያትነት ይጠቀሳል።  

በባህልና ጥበባት ዘርፍ የተቀናጀ አሰራር ባለመኖሩ የተስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂነት ያለው የባህል ልማት ለማምጣት እንዲቻል የምክር ቤቱ መቋቋም ዋነኛ ነጥብ ተደርጎ እንደሚወሰድ ይጠቀሳል። 

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህግ ባለሙያ አቶ ፍቅረሥላሴ ጌታቸው ረቂቅ ደንቡን ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በባህልና ጥበብ ዘርፍ የተቀናጀ አሰራር እንዲኖር ያደርጋል።  

የጥበብ ባለሙያዎች ከስራዎቻቸው ሊያገኟቸው የሚገባቸውን የሞራልና ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ለማስጠበቅ ያግዛል።

የጥበብ ባለሙያዎች የመንግስትን ድጋፍ የሚሽበት ሁኔታ እንደነበረ ያስታወሱት፤ ምክር ቤቱ ሲቋቋም መንግስት በተደራጀ መልኩ ድጋፍ ለመስጠት እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የአገር ውስጥና የውጪ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱን ለመቋቋም የቀረበው የረቂቅ ደንብ ለአገሪቷ የባህልና ጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

''የሽልማት ድርጅት በዚህ ዘርፍ ውስጥ መካተት ነበረበት በፊት ኢትዮጵያ በአፍሪካና በአለም ጠንካራ የሽልማት ድርጅት ነበራት ፣ በርካታ ተመራማሪዎችን ሸልማ ታውቃለች። ስለዚህ ይህ በደንቡ አልተካተተም” በማለት ነው በረቂቅ ደንቡ ላይ መካተት አለበት ያሉትን ሀሳብ ያነሱት።

የሴት ሰዓሊያን ማህበር ፕሬዝዳንት ሰዓሊ ሩት አድማሱ፤ የምክር ቤቱ መቋቋም አጠቃላይ የጥበብ ባለሙያውን ለመደገፍ እንደሚያስችል ያምናሉ።

በተለይ የኪነ ጥበብ ሰዎችን "እውቅና ከመስጠት አኳያ የሽልማት ድርጅት ቢካተት የሚለውን ሃሳብ እኔም የምጋራው ነው" ብለዋል።

የባህልና ቱሪዚም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት እንደገለጹት ፤ ይህ በባህል ልማት ዘርፍ የሚቋቋመው ምክር ቤት በርካታ ጠቀሜታ አለው። አንድና ወጥ ሆኖ ኪነ ጥበብና ባህልን ተመጋጋቢ ከማድረግ፣ ከማጎልበትና ከማሳደግ አኳያ ሚና ይኖረዋል።

ባህልም ለኪነ ጥበብ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማስተሳሰርም ታስቦ የሚቋቋም መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ረቂቅ ደንቡን "ለማዳበር የሚያስችሉ በርካታ ሃሳቦች እየተገኙ  ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታ ብዙነሽ ፤ በሰነዱ ላይ በቂ ግብዓቶች ከተካተቱና ከጸደቀ በኋላ ምክር ቤቱ ተቋቁሞ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከምክር ቤቱ ጋር 26 የመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ታዋቂ ግሰቦች  በአጋርነት እንደሚሰሩም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም