የክልሉ ብሔረሰቦች በፌደራል ስርዓቱ ተጠቃሚነታቸው አድጓል---አቶ አሻድሊ ሃሰን

89
አሶሳ ግንቦት17/2010 የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ብሔረሰቦች በፌደራል ስርዓቱ ባገኙት ውክልና የልማት ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡ ርዕሠ መስተዳድሩ  27ኛው የግንቦት ሃያን በዓል አስመልክቶ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የፌደራል ስርዓቱ የክልሉን ብሔረሰቦች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተሳትፏቸው እንዲያደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ "የሀገሪቱ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት አንድነት አስጠብቆ ማስቀጠል የቻለ ነው" ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ላለው ፈጣንና ፍትሃዊ እድገት መሰረት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ብሔረሰቦች በፌደራል ስርዓቱ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ከጀመሩ ወዲህ በአካባቢው ከፍተኛ እድገት ሊመዘገብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ ከልሉ ሲመሰረት የነበረው የተማረ የሰው ኃይል፣ መሰረተ ልማት እንዲሁም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ "ባለፉት 27 ዓመታት በተከናወኑት የልማት ስራዎች በክልሉ የትምህርት፣ የጤናና የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተደራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል "ብለዋል፡፡ የክልሉን ህዝቦች የልማት ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግም ተበታትነው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመንደር በማሰባሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ተቋማት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ በተከናወኑት የልማት ስራዎች የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ይበልጥ ያሳደገ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አሻድሊ  አሁንም ትኩረት የተሰጣቸው የልማት ዘርፎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣ የከተሞች ልማት እንዲሁም የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል ይገኙበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደሩ የሚገኙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ሰፊ ርብርብ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡ የፌደራል ስርዓቱ ዜጎች በየትኛውም ቦታ ተዘዋውረው የመስራትና የመኖር መብት የሚያስጠብቅ በመሆኑ ክልሉ በርካታ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመቻቻልና በአንድነት የሚኖሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም