የጥቃቅንና አነስትኛ ዘርፍ ሞደል አምራቾች የሚሳተፉበት ኢግዚብሽንና ባዛር በመጪው ሰኞ ይከፈታል

63

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2011 በጥቃቅንና አነስትኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ በሞዴልነት የተመረጡ አምራቾች የሚሳተፉበት አገር አቀፍ ኢግዚብሽንና ባዛር በመጪው ሰኞ በአዲስ አበባ ይከፈታል።

የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጄንሲ የኮሚንኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ፈረደ በሰጡት መግለጫ ኢግዚብሽንና ባዛሩ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተሰማርተው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ አምራቾች ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበት ይሆናል።

መድረኩ ቋሚ የገበያ ትስስር ከህብረተሰቡ ጋር ከመፍጠር ባለፈ ከሌሎች አቻ ኢንተርፕራዞች ጋር የልምድ ልውውጥ ለመፍጠር ያግዛልም ብለዋል።

ለሰባት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ባዛር የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የከተማ ግብርና ውጤቶች፣ የእደ ጥበብና ቅርጻቅርጽ ስራዎችና ሌሎችም ምርቶች ይቀርባሉ።

እንደ አቶ አሰፋ ገለፃ ኢግዚብሽንና ባዛሩ ላይ ከዚህ በፊት ይስተዋል የነበረውን የራሳቸው ያልሆነ ምርት አቅራቢዎችን ለመቆጣጠር የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይመደባሉ።

በኢግዚብሽንና ባዛሩ ላይ 10 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና እንዲሁም 185 በጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የተሰማሩ አምራቾች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ከአቅራቢዎቹ መካከል 50 በመቶው ሴቶች ሲሆኑ 3 በመቶው ደግሞ አካል ጉዳተኞች ናቸው።

ኢግዚብሽንና ባዛሩ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በመጪው ሰኞ በሚከፈተውና ለሳምንት በሚቆየው የመጀመሪያው ዙር ላይ 17 ሺህ የሚደርሱ ሸማቾች ተገኝተው ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።

እግዚቢሽንና ባዛሩ ''ተወዳዳሪ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማፍራት የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥ እናፍጥናለን'' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ዋቤ ሸበሌ ሆቴል ጎን ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም