በጋሞ ጎፋ ዞን ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር ከመኸር ልማት ተገቢውን ምርት እንዳናገኝ አድርጎናል - አርሶ አደሮች

41

አርባምንጭ ታህሳስ 19/2011 በጋሞ ጎፋ ዞን በቅርቡ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር ከመኸር እርሻ ልማት ተገቢውን ምርት ማግኘት እንዳላስቻላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ  አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

ሰላማዊ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በመስመር መዝራትን ጨምሮ ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን በመጠቀም ጥሩ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ካምባ ወረዳ ዶምቤ ሰሮ ቀበሌ አርሶ አደር ዮሐንስ ጋሞ በሰጡት አስተያየት በአከባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት የመኸር የእርሻ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን ባመለቻላቸው የሰበሰቡት ምርት የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡

ባለፈው ዓመት ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳ 15 ኩንታል ቦሎቄ ማግኘታቸውን አስታውሰው ዘንድሮ ግን በችግሩ ምክንያት ከተመሳሳይ ማሳ የሰበሰቡት ስድስት ኩንታል ምርት ብቻ ነው፡፡

በቀበሌው በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ የዘሩትን ጤፍ ባለመከታተላቸው ሙሉ በሙሉ ምርት ሳይሰጥ መቅረቱን የተናገሩት ደግሞ የመለኮዛ ወረዳ አርሶ አደር አስናቀች ከማ ናቸው ፡፡

ከመኸር የግብርና ሥራ ምንም ምርት ባለማግኘታቸው በኑሮአቸው ላይ  አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን ጠቅሰዋል ፡፡

በአንጻሩ የምዕራብ ዓባያ ወረዳ ፉራ ቀበሌ አርሶ አደር ማቴዎስ ማንቺካ በሰጡት አስተያየት አከባቢው ሰላም በመሆኑ ከ2 ሄክታር ማሳቸው 72 ኩንታል የበቆሎ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመስመር መዝራትን ጨምሮ  ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን በመጠቀማቸው ጥሩ ምርት ማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

የግብርና ባለሙያዎችም በቅርበት ልማቱን በመከታተል የሚሰጡት ሙያዊ ድጋፍ  ለምርታማነታቸው ትልቁን አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጋሻሁን ሞላ በበኩላቸው በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት በመኸር እርሻ ልማት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልፀዋል፡፡

በ2010/11 የመኸር እርሻ ሥራ በ15 የገጠር ወረዳዎች 206 ሺህ 404 ሄክታር ማሳ ለማልማት የታቀደ ቢሆንም ማልማት የተቻለው 126 ሺህ 738 ሄክታሩን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግብአት አጠቃቀምን በተመለከተም ለመኸር ልማት ለመጠቀም ከታቀደው 262 ሺህ ኩንታል ዩሪያና ዳፕ ማዳበሪያ ውስጥ ጥቅም ላይ ማዋል የተቻለው ከ36 ሺህ ኩንታል አይበልጥም፡፡

የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ድጋፍ መስጠት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በምርት ዘመኑ ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ቢታቀድም ከቅድመ ምርት ትንቢያ በተረጋገጠው መረጃ መሠረት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 15 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ነው፡፡

መንግስት በቅርቡ ከአስተዳደር መዋቅር ጋር በተያያዘ ያለውን የዞኑን ችግር ከፈታ ወዲህ አንጻራዊ ሰላም የተገኘ በመሆኑ በመኸር የታጣውን ምርት በመስኖ ለማካካስ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

በዞኑ በ2009/2010 የምርት ዘመን ከ22 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም