የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ህጎችን በአንድ የመረጃ ቋት የያዘ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

1715

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2011 የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኢትዮጵያ ከ1934 እስከ 2010 ዓ.ም የወጡ ህጎችን በአንድ የመረጃ ቋት አጠቃሎ የያዘ መተግበሪያ (ሶፍት ዌር) ይፋ አደረገ።

ለተቋሙ ተጠሪ የሆነው የፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲም 19 ዓይነት የውክልና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የመተገበሪያ መሳሪያም ይፋ አድርጓል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ስለመተግበሪያዎቹ አጠቃላይ ገለፃ በማድረግ ስራው በይፋ መጀመሩን አብስረዋል።

በዚህ ጊዜ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ እንደገለጹት ተቋሙ ከ1934 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም በአገሪቱ የወጡ የክልልና የፌዴራል መንግስት ህጎችን በአንድ የመረጃ ቋት የሚያጠቃልል መተግበሪያ መሳሪያ ፈጥሯል።

መተግበሪያው እስካሁን በአገሪቷ የወጡትን ሕጎችና የሰበር ውሳኔዎችን ጠበቆች፣ፖሊሶች፣ዳኞች፣ዐቃቤ ህጎች፣ ምሁራን፣ተመራማሪዎችና ህብረተሰቡ ያለ ኢንተርኔት አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

አስገዳጅ የሆነ የህግ ትርጉም ያላቸውን የሰበር ውሳኔዎች በቀጥታ በማቅረብ በአንድ ቦታ ላይ ቀላልና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ አዋጅና ደንቦችን ለማቅረብ ያስችላልም ብለዋል።

ይህም የህግ መረጃን ተደራሽነት ለማረጋገጥ፣ የዜጎች የህግ እውቀት ለማዳበርና የህግ ማስከበር ሥራዎች በተሟላ መልኩ ለማከናወን ያግዛል ነው ያሉት።

ሶፍት ዌሩ መሻሻል እየተደረገበት የተጨማሪ ዓመታትን መረጃ እንድይዝ የሚያደረግ መሆኑንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስረድተዋል።

የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መረሳ ገብረዮሃንስ በበኩለቻው ኤጀንሲው የተገልጋዩን ፍላጎት መሰረት በማድረግና የዳሰሳ ጥናት በመካሄድ 19 አይነት አገልግሎቶችን በኦን ላይን ለመስጠት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

አሁን ይፋ የተደረገው መተግበሪያም ተገልጋዮች የሚያባክኑትን ጊዜ፣ወጪ፣ ምልልስና የውክልና ጉዳዮችን በመሙላት መጭበርበርን የሚያስቀር መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም ተደራሽነትንና የሰነድ ጥራትን በማረጋገጥ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ቀላልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ መረሳ ገለፃ የኦንላይን አገልግሎቱ ጠቅላላና ልዩ ወክልና ፣ የቤተሰብና የጠበቃ ውክልና፣የሚንቀሳቀሱና የማይነቃቀሱ የሽያጭ ውሎች ይከናወንበታል።

በተጨማሪም የሚንቀሳቀሱና የማይነቃቀሱ የስጦታ ውሎች፣የውክልና መሻሪያ ሰነዶችና ውል ቀሪ ማድረጊያ ሰነዶች አገልግሎት ይሰጥበታል ብለዋል።

አገልግሎቱ በቀላሉ የሚገኝና የሚሞላ፣ ፈጣን፣ በአንድ ጊዜ ብዙ ጉዳዮችን ለመስራት የሚያስችል፣ የመረጃ ደህንነቱም የተጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።

የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በአገሪቷ 15 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያሉት ሲሆን በቀን 7 ሺህ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ እየሰራ ይገኛል።