በትግራይ የተገነቡ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት የተሟላ አገልግሎት እንደማይሰጧቸው ወጣቶች ተናገሩ

72

መቀሌ ታህሳስ 19/2011 በትግራይ ክልል የተገነቡ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት የተሟላ አገልግሎት እንደማይሰጡ ወጣቶች ገለጹ።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ የማዕከላቱን ችግሮች እፈታለሁ ይላል።

ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወጣቶቹ እንዳስረዱት ማዕከላቱ በሚሰጡት አገልግሎት የወጣቶችን ፍላጎት የማይመጥን በመሆኑ እርካታ አጥተውባቸዋል።

የሁመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኃይለየሱስ ሰለሞን ማዕከሉ የተሟላ ቤተመፃህፍት፣የአቻ ለአቻ መወያያ አዳራሽና የስፖርት ግብዓቶች እንዳልተሟሉለት ይገልጻል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ግንባታው የተጠናቀቀው ማዕከል ከ30 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ሥራ ይፈጥራል ተብሎ ሲጠበቅ፤ ይልቁንም ለግለሰብ በኪራይ መሰጠቱንተናግሯል፡፡

የዓዲግራት ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ክብሮም አማረ በበኩሉ በከተማው የተገነባው ማዕከል ቴሌቪዥን፣ኮምፒዩተሮችና የውጭ መጫወቻ ቁሳቁስ አልተሟሉለትም ብሏል።

በዚህም ወጣቶች ከእፅና ከአልኮል ነፃ ሆነው ጊዜያቸውን በመልካም ሁኔታ ለማሳለፍና ትምህርት ለመቅሰም እንዳላስቻላቸው ገልጿል።

በከተማው ውስጥ የሚገኙ ሁለት ማዕከላት በተሟላ መልኩ ሥራ በመጀመራቸው ጊዜያችንን እያሳለፍንባቸው ነው በማለት አስተያየቱን የሰጠው የዓድዋ ከተማ ነዋሪ ወጣት የማነ ተስፋይ ነው።

የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኪሮስ ንጉስ ተጠይቀው እንዳሉት፣በክልሉ ከተገነቡት ማዕከላት 46ቱ የቤተ መጻህፍት፣ኮምፒዩተሮች፣የአቻ ለአቻ ምክክር የሚካሄድባቸው ቁሳቁስ እንዳልተሟሉላቸው ተናግረዋል።

በአገልግሎት አሰጣጣቸው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ማዕከላት ደረጃ ለማሳደግ ግብአቶችን ለማሟላት ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።

እስካሁንም ከ30 በላይ የሚሆኑ ኮምፒዩተሮች በዕርዳታ መገኘታቸውንና በቀጣዮቹ በስድስት ወራትም እጥረቱን እንደሚፈታ ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

በክልሉ 82 የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም