በአማራ ክልል በ2 ሺህ 948 ሄክታር መሬት የበቆሎ ማሳ ላይ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየተሰራ ነው

63
ባህርዳር ግንቦት 17/2010 በአማራ ክልል በመስኖ ከለማው የበቆሎ ሰብል 2 ሺህ 948 ሄክታሩ በአሜሪካ መጤ ተምች መወረሩንና ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ታሪክ ለኢዜአ እንደገለፁት መጤ ተምቹ ካለፈው ወር ጀምሮ በ10 ዞኖች በሚገኙ 31 ወረዳዎች በመስኖ በለማ የቆሎ ሰብል ላይ ተከስቷል። በተለይም በመዕራብ ጎጃም- ጃቢጠናንና ወንበርማ ወረዳዎች፣ በሰሜን ጎንደር - ጎንደር ዙሪያና ታች አርማጭሆ ወረዳዎች፣ ምስራቅ ጎጃም- ደብረ ኤሊያስና ማቻከል ወረዳዎች፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን- አየሁ ጓጉሳና ጓንጓ ወረዳዎች መከሰቱን ገልጸዋል። ተምቹን ለመከላከል ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅቶ አርሶ አደሩንና የግብርና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል። ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በተከናወነ የመከላከል ሥራ 1ሺህ 157 ሄክታር ላይ ያለውን የበቆሎ ማሳ በባህላዊ መንገድና ኬሚካል በመርጨት ከተባዩ ለማጽዳት መቻሉን አቶ ጌትነት ተናግረዋል። "መጤ ተምቹ ከመስኖ ምርት ባለፈ በቀጣይ በመኸር ወቅት ወደሚለማው ሰብል እንዳይዛመት አርሶ አደሩ ከወዲሁ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር በየቀኑ ማሳውን በመዳሰስ የመከላከል ሥራውን ማጠናከር አለበት" ብለዋል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉጌታ አስቻለው በበኩላቸው በመስኖ ያለሙት አንድ ሄክታር በቆሎ ሙሉ በሙሉ በአሜሪካ መጤ ተምቹ መወረሩን ተናግረዋል። ተምቹ ቀን ፀሐይ ሲነካው እራሱን እንደሚደብቅና ሌሊት በመስፋፋት በወረርሽኝ መልክ እየተዛመተ መሆኑን ገልፀዋል። ያለሙትን የበቆሎ ሰብል ሙሉ በሙሉ የወረረውን ተምች በባህላዊ መንገድ መከላከል ባለመቻላቸው ፀረ ተባይ ኬሚካል በመጠቀም ለማጥፋት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። በግማሽ ሄክታር በቆሎ ማሳቸው ላይ የተከሰተውን ተምች ኬሚካል በመርጨት እየተከላከሉ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በማቻከል ወረዳ የውላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሽታ ፀጋ ናቸው። "ከተምቹ በፍጥነት የመባዛት አስቸጋሪ ባህሪ ጋር በተያያዘ አርሶ አደሮች መተባበርና በጥንቃቄ ልንከታተለው ይገባል፤ ይህ ካልሆነ አስቸጋሪ ነው" ብለዋል። ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን በክልሉ በሚገኙ ስድስት ዞኖች ተምቹ ተከስቶ ከወረረው 98 ሺህ በላይ ሄክታር በቆሎ ከ89 በመቶ በላይ ሄክታሩን መከላከል እንደተቻለ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያስረዳል። መነሻው ከደቡብ አሜሪካ አገራት እንደሆነ የሚነገርለት አሜሪካ መጤ ተምች ከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪካ በቆሎ በሰፊው በሚያመርቱ ናይጀሪያ፣ ቤኒንና ቶጎ አርሶ አደር ማሳ ላይ የተገኘ ሲሆን በአገራችንም ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል ተከስቶ ሁሉንም በቆሎ አምራች ክልሎች ማዳረሱ ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም