በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ነው

120

ነገሌ ታህሳስ 19/2011 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ባለፉት አራት ወራት በባህላዊ መስኖ ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

በዘር የተሸፈነው መሬት በዞኑ በተያዘው በጋ በመጀመሪያ ዙር በመስኖ ለማልማት በእቅድ ከተያዘው 32 ሺህ 649 ሄክታር መሬት ውስጥ ነው፡፡

በባለስልጣኑ የመስኖ ውሀ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ኤልያስ መኮና እንዳሉት እስካሁን በተካሄደው የመስኖ ልማት ስራ 21 ሺህ 948 ሄክታር መሬት በተለያየ ዘር ተሸፍኗል፡፡

ቀሪውን መሬት የማልማት ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ምርታማነትን ለማሳደግም 3 ሺ 484 ኩንታል ምርጥ ዘርና የፋብሪካ ማዳበሪያ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አብራርተዋል፡፡

ከመጀመሪያ ዙር ባህላዊ መስኖ ልማት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ የመስኖ ልማት ስራ በመሳተፍ ላይ ካሉ 56 ሺ 397 አርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች መካከል 13 ሺ 384ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

በጉጂ ዞን ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥር 30 አንደኛ ዙር ከየካቲት እስከ ሀምሌ መጨረሻ ደግሞ ሀለተኛ ዙር የመስኖ ልማት ወቅት እንደሆነ ከባለሙያው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዞኑ ዋደራ ወረዳ የጨቆርሳ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ማሙሽ ጨኖ በአንደኛው ዙር መስኖ ልማት ከ45 ኩንታል በላይ የጎመን፣ ካሮት፣ ሽንኩርትና ቀይ ስር ምርት ለመሰበሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

''በመስኖ ለማልማት ካዘጋጀው ሁለት ሄክታር መሬት እስካሁን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን በተለይ በጎመንና በቀይ ስር ዘር ተሸፍኗል'' ብሏል፡፡

የመስኖ ልማት የዘር ስራውን ከሁለት ሳምንት በኋላ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ በሳምንት ሶስት ቀን ውሀ በማጠጣት እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡

ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ በየነ ኦዳም ''ለመስኖ ልማት ከ3 ሄክታር የሚበልጥ መሬት  አዘጋጂቻለሁ'' ብለዋል፡፡

ለመጀመሪያው ዙር ያዘጋጁት መሬት በአብዛኛው በቀይ ስር፣ ካሮትና ጥቅል ጎመን ዘር የተሸፈነ በመሆኑ የጥበቃና ክብካቤ ስራ እንደሚጠብቃቸው ጠቁመዋል፡፡

''አሁን ላይ የምሰበስበውን የምርት መጠን መተንበይ አልችልም' ያሉት አርሶ አደሩ 'ጉልበቱን ሳይቆጥብ በርትቶ የሰራ ጥሩ ምርት ያገኛል'' ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም