የሐረሪ ክልል መንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት እንደሚሰጥ ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋገጡ

104

ሐረር ታህሳስ 19/2011 የሐረሪ ክልል መንግሥት ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት እንደሚሰጥ ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋገጡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪና የክልሉ መንግሥት ካቢኔ አባላት መጓተት የሚታይባቸውን ፕሮጀክቶችን ትናንት ጎብኝተዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታን መፍጠራቸውን ያወሱት አቶ ኦርዲን፣ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳና በውሉ መሠረት ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት ክትትልና ቁጥጥሩን ያጠናክራል ብለዋል።

በተለይ ለወጣቶች ሥራ የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ጉብኝቱ ከሪፖርት ባለፈ በተጨባጭ እየተከናወኑ ያሉትን ሥራዎች ውጤት ለመመልከት፣ ለመገምገምና ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል። 

በርዕሰ መስተዳድሩ በሚመራው ቡድን ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል በ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የአው አባድር ዘመናዊ ስታዲዬም አንዱ ነበር።

በሦስት የግንባታ ደረጃዎች ተከፋፍሎ የሚገነባው ስታዲዬም 85 በመቶ የደረሰ ቢሆንም፤ግንባታው የተጀመረው ከ2008 መጨረሻ ከመሆኑ አኳያ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ እንደነበረበት ተገልጿል።

የአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ተወካይ መሐንዲስ እስጢፋኖስ ይመር የስታዲዬሙ ግንባታ በብረት ዋጋ መናርና በፋይናንስ እጥረት  መጓተቱን  ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነቡ ያሉት የቴክኒክና ሙያና የነርሲንግ ኮሌጆች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የክልሉ የፍትህ ቢሮ ሕንጻ ግንባታ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ቤቶች ልማትና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ኢሊ አብዱረሂም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም