በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አሁንም ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች አሉ - ተገልጋዮች

80
ዲላ ግንቦት 17/2010 የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል በአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ያልተቀረፉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ተገልጋዮች ገለፁ ፡፡ ሪፈራል ሆስፒታሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከተገልጋዮች ጋር ተወያይቷል ፡፡ በውይይት መድረኩ የተሳተፉ ተገልጋዮች እንደተናገሩት ቀደም ሲል  በነበሩ የውይይት መድረኮች በሆስፒታሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ  ያነሷቸው ችግሮች መሻሻል እያሳዩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ  አሁንም ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ የዲላ ከተማ ነዋሪ አቶ ኤፍሬም ግርማ በሰጡት አስተያየት በሆስፒታሉ ቀደም ሲል የነበረው የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት ችግር አሁን መቀረፉ መልካም ጅምር ነው፡፡ አሁንም ግን ሆስፒታሉ የአይን ህክምና አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ በግል የህክምና ተቋማት በመታከም ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ በተጨማሪም የሆስፒታሉ አንዳንድ የአስተዳደር ሰራተኞችና የጤና ባለሙያዎች ተገልጋዮችን የማመናጨቅ ችግር በስፋት እንደሚስተዋልባቸው ገልፀዋል ፡፡ ሌላው የዲላ ከተማ ነዋሪ አቶ አበባየሁ ገብሩ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ካርድ ክፍል ያለው ግርግርና በወረፋ ያለመስተናገድ ችግር ህሙማንን እያማረረ በመሆኑ ሊፈተሽ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የነፃ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎችም ከምግብና አልጋ ውጪ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የሆስፒታሉ መድኃኒት ቤት የተሟላ አቅርቦት ስለሌለው ከግል መድኃኒት ቤቶች በውድ ዋጋ ለመግዛት እየተገደዱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከወናጎ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ታየች አየለ ደግሞ ሆስፒታሉ የእናቶች ቅድመ ወሊድ ክትትልና የማዋለድ አገልግሎት መሻሻል ቢታይበትም ከወሊድ በኋላ የእናቶች ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጉድለት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ የሆስፒታሉ መፀዳጃ ቤትና የግቢው ንፅህና ባለመጠበቁ ለታካሚዎና አስታማሚዎች የወባና የሌሎች በሽታዎች ምንጭ እየሆነ ነው፡፡ በሆስፒታሉ የህክምናና ተግባር ሥልጠና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ቤዛ ''ህብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ ያለውን ክፍተት ነቅሶ መናገሩ ችግሩን ለመፍታት እንድንተጋና ተጨባጭ ለውጥ እንድናመጣ ይረዳናል'' ብለዋል ፡፡ የተነሱ ችግሮችን የሆስፒታሉ አስተዳደር በጋራ ገምግሞ የመፍትሔ እርምጃ እንደሚወስድ የገለፁት ዶክተር አሸናፊ በተለይ የባለሙያዎች ሥነ-ምግባርን በተመለከተ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስረድተዋል ፡፡ ዶክተር አሸናፊ እንዳሉት በዚህ ረገድ ሆስፒታሉ ለሁሉም ባለሙያዎች ተግባርን መሰረት ያደረገ ሥልጠና እያዘገጀ ሲሆን የሥነ-ምግባር ጥሰት በሚታይባቸው ባለሙያዎች ላይ አስፈላጊው እርምጃ ይወስዳል ፡፡ የመፀዳጃ ቤትና የግቢውን ንፅህና ችግርም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ገልፀው ሆስፒታሉ ባሉት አልጋዎች በሙሉ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ለማሰገባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የሆስፒታሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተስፋነው በቀለ በበኩላቸው ''የውይይት መድረኩ አገልግሎት አሰጣጣችንን ለማሻሻል ከምናከናውናቸው ተግባራት አንዱ ነው'' ብለዋል ፡፡ ''አምና በነበረው መድረክ የሆስፒታሉ መድኃኒት አቅርቦት እና የላብራቶሪ እጥረት በስፋት ተነስቶ ነበር'' ያሉት ደክተር ተስፋነው በተለይ የላብራቶሪ አቅሙን በማሳደግ የሚሰጡ የምረመራ አይነቶችን ከ16 ወደ 70 ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል ፡፡ የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎንም ተደራሽነትን ለማስፋት በከተማው ሁለት ተጨማሪ መድኃኒት ቤቶች እንደሚከፈቱ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም