ፍርድ ቤቱ በነብርጋዴል ጀኔራል ጠናው ቁርንዲ መዝገብ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት የተጠየቀውን ጊዜ ፈቀደ

772

አዲስ አበባ ታህሳስ 18/2011 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት በነብርጋዴል ጀኔራል ጠናው ቁርንዲ መዝገብ በከባድ የሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት የተጠየቀውን ጊዜ ፈቀደ።

ጠቅላይ አቃቢ ህግ አንደኛ፣ ሁለተኛ፣አራተኛ፣ስድስተኛ፣ ስምንተኛ ፣ ዘጠነኛ፣ አስራ አንደኛ፣አስራ ሁለተኛ፣ አስራ ሶስተኛ እና ሃያኛ ተጠርጣሪዎች ላይ የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የክስ መመስረቻ ጊዜ የተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል የዋስትና መብት የሚከለክል በመሆኑ የዋስትና መብታቸው ታግዶ ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ምርመራ በመጨረሱ የአስራ አንዱም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበር አለበት የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።

በመቀጠልም የተፈቀደው የክስ መመስረቻ ጊዜ ረጅም በመሆኑ እንዲቀነስ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።