ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን እንደሚደግፉ በምስራቅ ወለጋ የኪረሙ የትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ

53

ነቀምቴ ታህሳስ 18/2011 ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ  የኪረሙ ሁለተኛና መሰናዶ የትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ፡፡

ተማሪዎቹ  ሰላማዊ የትምህርት እንቅስቃሴን ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ከአካባቢው አመራሮች ጋር  ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት የትምህርት ቤቱ የ12ኛ ከፍል ተማሪ ደሜ ዘላለም በሰጠው አስተያየት ከትምህርት ቤቱ ጋር ባደረጉት ምክክር ተማሪዎች የሁከት ፈጣሪዎችን ወሬ ባለመስማት   ትምህርታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመቀጠል መስማማታቸውን  ተናግረዋል፡፡

ትምህርታቸውን እንዲያቆሙ የሚያደርጉ ቅስቀሳ  በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደለሌውና ትምህርት ለደቂቃ እንኳ መቆም እንደሌለበት ተማሪው ገልፀዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሥራን ማቆም ሀገርንና ሕዝብን መጉዳት በመሆኑ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ በአግባቡ መቀጠል እንዳለበት የተናገረው ደግሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ፈቀደ ዓለማየሁ ነው፡፡

" ትምህርትን ማቋረጥ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም " ያለው ተማሪ ፈቀደ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተማሩ ለራሳቸውና ለህብረተሰቡ መብት መታገል እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

ተማሪ አየሉ ክትል በበኩሏ መማር  ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣት እንደሆነ ገልጻ "ከተማርን ለሀገራችንና ለወገናችን እንጠቅማለን ፣ካልተማርን ግን የሀገር ሸክም ሆነን እንቀራለን" ብላለች፡፡

ለውጡንና ልማትን ማስቀጠል የሚቻለው በመማር እንጂ  ትምህርት ቤት በመዝጋት እንዳልሆነ ያመለከተችው ተማሪዋ ትምህርታቸውን ለደቂቃ  ቢሆን ላለማቋረጥ ተስማምተው እየተማሩ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ተሾመ ነሞ በበኩላቸው በትምህርት ቤታቸው የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዳይቋረጥ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በተደረገው ጥረት የትምህርት ጊዜ ሳይባክን መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

የኪረሙ ወረዳ የአባ ገዳዎች ጉባኤ ሰብሳቢ አባገዳ በቀለ ጅራታ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ማቆም፣መንገድ ፣ሱቅ ፣እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መዝጋት ህዝብና ሀገርን እንደሚጎዳ በመምከር ስራዎች እንዲጀምሩ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶችም በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ መፍታት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡

የወረዳው ትምህርት ቤቶች ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ፍቃዱ ባለፈው ሰኞ ተማሪዎች ክፍል ገብተው መማር እንደጀመሩ ለማወክ የመጡ ግለሰቦች ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ገብተው ችግር ለመፍጠር ሞክረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም ተማሪዎቹ እኛ በምንም ዓይነት ትምህርታችንን ማቋረጥ አንፈልግም ብለው እንዳስወጧቸውና ትምህርታቸውን በሠላማዊ መንገድ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

በየቦታው እየታየ ያለው የስራ ማቆም ለመመለስ ከሀገር ሽማግሌዎች ፣ኃይማኖት አባቶች፣አባ ገዳዎች እና በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተወካዮች ጋር መመካከራቸውን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ  አቶ በላይ ደሣለኝ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ስራ መቆም እንደሌላበት መግባባት ላይ በመድረስ የተዘጉ ሱቆችና፣ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲከፈቱ በማድረግ ሁሉም ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

የኪረሙ ሁለተኛና መሰናዶ የትምህርት ቤት ተማሪዎች በምዕራብ ኦሮሚያ ስራ ለማቆም ባለው እንቅስቃሴ ባለመሳተፍ ጸንተው ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ የቀጠሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም