ምክር ቤቱ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በማስጠበቅ ረገድ ሃላፊነቱን እንዳልተወጣ አንድ ምሁር ገለፁ

108

አዲስ አበባ ታህሳስ 18/2011 የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በማስጠበቅ ረገድ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት አለመወጣቱን አንድ ምሁር ገለፁ።

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ "በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሴቶች ሚና" በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ፕሮፌሰሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህገ መንግስቱን የሚፃረሩ፣የዜጎችን ክብር፣ ሰላምና የአገሪቱን ደህንት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ከመከላከል አንፃር በአግባቡ ሃላፊነቱን አልተወጣም።

እንደ ፕሮፌሰር ካሳሁን ገለፃ ባለፉት ዓመታት በአገሪቷ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፍትህ  አሰጣጥ ስርዓት መዛባት “ያለ ልጓምና ከልካይ" ተስፋፍቶ ቆይቷል።

የምክር ቤቱ አባላትም ከህዝብ ይልቅ ለፓርቲያቸው ያላቸውን ታማኝነት በማስበለጥ የህዝብን ድምፅ "ጆሮ ዳባ ልበስ" ብለው ቆይተዋል ነው ያሉት።

አባላቱ ይህንን ማድረግ ያልቻሉት የፍትህና የአስፈጻሚ አካላት የፖለቲካ ተጽዕኖ፣ጣልቃ ገብነትና የገዢው ፖርቲና የመንግስት አሰራር መቀላቀልና ሌሎች ጫናዎችን መቋቋም ባለመቻላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም የምክር ቤቱ አባላት የህግ የበላይነትን የማስከበርና ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን የመግታት አቅም እንዳይኖራቸው ሆኗል ብለዋል።

ይሁን እንጂ በቅርብ ወራት ውስጥ በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ምክር ቤቱ የህዝብ እንደራሴነቱን ሃላፊነት በአግባቡ ይወጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የሰላም እጦት ውሎ አድሮ የሁሉንም ቤት ማንኳኳቱ የማይቀር በመሆኑ "በዝምታ" የመፍትሄው አካል በመሆን መስራት አለብን ብለዋል።

ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሴቶች የነበራቸውን ታሪካዊ ዳራያወሱት ፕሮፌሰሩ አሁንም ያሉትን መልካም እድሎች በመጠቀም ሰላም በማስፈን ረገድ ያላቸውን ችሎታ ማሳየት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ አገሬ ምናለ እንደገለፁልን ባለፉት ጊዜያት ምክር ቤቱ ሃላፊነቱን በመወጣት በኩል ውሱንነቶች እንደነበሩበት ተናግረዋል።

በተለይም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በማስቆም በኩል ሃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ፀፀት እንደተሰማቸው አልደበቁም።

እንደ ወይዘሮ አገሬ ገለፃ በእርሳቸው የምክር ቤት ስራ ዘመን በርካታ ስራዎችን መስራት የሚቻልበት ጊዜ ቢያልፍም በቀሪው ጊዜ ግን በሙሉ አቅማቸው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ዳንኤል ዴቦ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የአቅም ውስንነት ችግር እንደነበረበትና ሀላፊነቱን በአግባቡ ያለመወጣቱንም ጠቅሰዋል።

ዜጎች ላይ ሲፈፀሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ መረጃ እንዳልነበራቸው ገልጸው በቀጣይ የህዝቡን ችግሮች በቅርበት በመከታተል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጨፎ  በበኩላቸው የምክር ቤቱ አባላት የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅና የለውጥ ሂደቱን በመደገፉ "ግንባር ቀደም" ሆነው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም