በደሴ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ የምግብ ዘይት ተያዘ

53

ደሴ ታህሳስ 18/2011 በደሴ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ዘይት መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ዘይቱ የተያዘው ዛሬ ረፋዱ ላይ በታርጋ ቁጥር ኮድ 3- 51339 ኢት አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ  ከከተማው ለጊዜው ወዳልታወቀ ስፍራ ለማጓጓዝ ሲሞከር ነው፡፡

ፈቃድ ሳይኖረው በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የተገኘው የምግብ ዘይት በታሸጉ ጄሪካኖች ውስጥ የነበረ 21 ሺህ ሊትር  መሆኑን  በደሴ የከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ  የአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ዘሩ ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡

ኢንስፔክተሩ እንዳሉት በአሽከርካሪው ሁኔታና ድርጊት ጥርጣሬ ያደረባቸው የደሴ ከተማ መናፈሻ አካባቢ ነዋሪ ወጣቶች ለፖሊስ በሰጡት  ጥቆማ  ሊያዝ ችሏል፡፡

አሽከርካሪው  ከአካበባቢው ለመሰወር ቢሞክርም በወጣቶች  ትብብርና ክትትል ተይዞ  ጉዳዩ በመጣራት ላይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ወጣቱ ህገ ወጥነትንና ወንጀልን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ  መሆኑን ያስታወቁት ኢንስፔክተሩ  ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም