በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረትና ኢፍትሃዊነት ተቸግረናል - የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች

124

ሶዶ ታህሳስ 18/2011 በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረትና ፍትሃዊነት የጎደለው ስርጭት መቸገራቸውን የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

የከተማዋ አሰተዳደር በበኩሉ የነዋሪዎች ቅሬታ ትክክል መሆኑንና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ተግባር መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በከተማዋ የመርካቶ ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ አማረች ሃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸውን የፍጆታ እቃዎች በተለይ ስኳር በተገቢው ጊዜ ማግኘት አልቻሉም፡፡

በዚህም ከነጋዴዎች ሶስት እጥፍ የዋጋ ጭማሪ በመግዛታቸው ''ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር  እየዳረገን ነው'' ብለዋል፡፡

ሌላኛው አሰተያየታቸውን የሰጡ የዋዱ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከድር መሃመድ በበኩላቸው ዘይት በየወሩ ስኳር ደግሞ በየ45 ቀናት ለመውሰድ ኩፖን ቢወስዱም ወጥነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ከሰባት ወራት በላይ ችግሩን በተደጋጋሚ ለከተማ አስተዳደሩ   ቢያሳውቁም በቂ ምላሽ እንዳላገኙ የተናገሩት የጊዶ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ መስከረም እንዳለ ናቸው፡፡

''በዘርፉ የተሰማሩ ፈቃድ የተሰጣቸው ሸማች ማህበራት በህገ-ወጥ መልክ ለሚቸረችሩ ነጋዴዎች እያስተላለፉ ነዋሪውን እየበደሉት ነው፤ መንግስት ሊመለከተው ይገባል'' ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሰለ ሶርሳ ስለጉዳዩ  ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከነዋሪዎች የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

''የአቅርቦት ችግሩ የተፈጠረው የክልሉ መንግስት የከተማ ነዋሪውን ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት በ2004 የሰጠው ተመን ባለመሻሻሉና የነዋሪው ቁጥር በመጨመሩ ነው'' ብለዋል፡፡

የፍጆታ እቃዎችን ለነዋሪው ለማዳረስ ሲባል በግለሰብ ደረጃ የተመደበውን የኮታ መጠን ዝቅ ለማድረግ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከክልሉ መንግስት ጋር የነዋሪውን ቁጥር ያገናዘበ ተመን ለማውጣት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በህጋዊ የስራ ፈቃድ ህገ-ወጥ ተግባር በመፈጸም የፍጆታ እቃዎቹ ለነዋሪው እንዳይደርሱ  የሚያደርጉ ሸማች ማህበራት ና ነጋዴዎችን ስርዓት ለማስያዝ የኦዲትና የህዝብ ውይይቶች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ባለፈው ሳምንት በተደረገ የኦዲት ስራ አንድ ማህበር 2 ኩንታል ስኳር ደብቆ ለህገ-ወጥ ነጋዴዎች ማስተላለፉ በመረጋገጡ ከመስመሩ እንዲወጣና ነጋዴውን ጨምሮ እጃቸው ያለባቸው ግለሰቦች ላይ የማጣራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ ከ90 በላይ መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ለነዋሪው የሚያቀርቡ ህጋዊ ሸማች ማህበራት የሚገኙ ሲሆን 2 ሺ 232 ኩንታል ስኳር በየወሩ፤ 24ሺ782 ሊትር ዘይት ደግማ በየ45 ቀኑ ለህብረተሰቡ እንደሚያደርሱ  ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም