በምዕራብ ሸዋ ዞን 58 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ነው

67

አምቦ ታህሳስ 18/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን 58 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ መስኖ ልማት ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከሚያካሂዱት የመስኖ ልማት የተሻለ ገቢ ለማግኘት  እየሰሩ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኢሉ ገላንና የዳኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ገልፀዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተክሌ ኢዶሳ ለኢዜአ እንዳሉት በዞን በመጀመሪያ ዙር የሚካሄደው የዘንድሮው የመስኖ ልማት ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ነው፡፡

እስካሁንም 32 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች በ58 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በበቆሎ  እያለሙ ነው፡፡ 

በዞኑ በሁለት ዙሮች በመስኖ ለማልማት በእቅድ ከተያዘው 100 ሺህ ሄክታር መሬት 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ  አቶ ተክሌ አስታውቀዋል።

በዞኑ የኢሉ ገላን ወረዳ የኢሉ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኮንን በጂጋ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ዝናብ ጠብቀው የሚያመርቱት ምርት ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመስኖ ልማት ስራ በመሰማራታቸው ተጨባጭ ውጤት እያገኙና በኑሯቸውም እየተለወጡ  መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከመኸር እርሻ በተጓዳኝ  የመስኖ ልማት ስራ እንደጀመሩ ያስታወሱት አርሶ አደሩ ባለፈው የምርት ወቅት በአንድ ሄክታር መሬት ካለሙት ቲማቲም ከ30ሺ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉትም ባገኙት ገቢም የሣር ክዳን ቤታቸውን በቆርቆሮ መቀየር ችለዋል፡፡ 

ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ቶሌራ አቤቤ ከዚህ ቀደም እሳቸውን ጨምሮ የቀበሌው አርሶ አደሮች ስለመስኖ ልማት ግንዛቤ በማጣታቸው ለረጅም ዓመታት ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በ2005 ዓ.ም በግብርና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሠረት የቀበሌው አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጊዜውም የክረምት ዝናብን ጠብቀው የሚያመርቱት ሰብል ከ10 እስከ 13 ኩንታል ምርት ብቻ ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በመስኖ ልማት ስራ ተሰማርተው ድንች፣ ቲማትም፣ ቃሪያ እና ጎመን በ2 ሄክታር ማሳቸው በማምረት በዓመት እስከ 50 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡

ባገኙት ገቢም በኢጃጂ ከተማ ባለ ሁለት ክፍል ቤት ከመስራት አልፈው 10ሺ ብር በባንክ መቆጠባቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዳኖ ወረዳ የድሬ አለዩ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መገርሳ ኦሊቃ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ያሉ ወንዞችን በመጥለፍ ባለፈው ዓመት  በመስኖ ልማት ካገኙት 43ሺ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የወረዳው የግብርና ባለሙያዎችም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን አርሶ አደሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

"በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከማካሂደው የመስኖ ልማት ከ25 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኛለሁ ብዬ እጠብቃለሁ " ያሉት ደግሞ የዳኖ ወረዳ አርሶ አደር ጸሐይ ኢጃራ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም