የአዳማን ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሰሩ የፖሊስ አባላት ገለጹ

77

አዳማ ታህሳስ18/2011 የአዳማን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በትጋት እንደሚሰሩ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አባላት ገለጹ፡፡ 

ከ400 በላይ የሚሆኑ የአስተዳደሩ ፖሊስ አባላት ትናንት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክረዋል ።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ደረጀ ሙለታ በምክክር መድረኩ  እንዳሉት  ከተማዋ በሁሉም አቅጣጫዎች መተላለፊያ ናት ።

ይህንኑ ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳማን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ ምንጩ የማይታወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ገንዘብ መተላለፊያና የጦር መሳሪያ ማስገቢያ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም በህብረተሰቡ ድጋፍና በፖሊስ አባላት ቁርጠኝነት መክሸፉን አስረድተዋል ።

በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአዳማ ከተማ ፖሊስ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ኮማንደሩ ተናግረዋል ።

በአስተማማኝ ደረጃ  የሚገኘው የአዳማ ከተማን ሰላም ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ እንደተለመደው ከፖሊስ ጎን በመቆም አካባቢውን በመጠበቅና የተለየ ነገር ሲያጋጥመው ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በምክክር መድረኩ ከተሳተፉ አባላት መካከል  ዋና ኢንስፔክተር ብርሃኑ ወርቁ በሰጡት አስተያየት "የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር ረገድ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ እየሰራን እንገኛለን "ብለዋል።

የህብረተሰቡን ደህንነትና ፀጥታ ማረጋገጥ ብሎም ሰላምን ማስጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳቸው መሆኑን ተገንዝበው ህብረተሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልግል እንደሚተጉ  ተናግረዋል ።

"በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች አሁን የሚስተዋሉ ሁከት፣ ዝርፊያና ግድያ በከተማችን ቦታ የላቸውም" ያሉት ኢንስፔክተሩ የአካባቢያቸውን አስተማማኝ  ሰላም  እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።

የክልሉን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በሀገሪቱ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ለማሳካት  የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ኮማንደር መልካሙ ደበላ ናቸው።

"የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ህብረተሰቡን ከጎናችን በማሰለፍ ህገ ወጥነትና የጥፋት ሴራን  ለማምከን እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረንን ግንባር ቀደም ሚና አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም