በከተማዋ የሚሰሩ የእግረኛ መንገዶች ማሻሻያ ፕሮጀክቶች እስከ ሰኔ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ - ከንቲባ ድሪባ

71
አዲስ አበባ ግንቦት 17/9/2010 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመረጡ ነባር መንገዶች ላይ እየተከናወነ ያለው የእግረኛ መንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ግንባታ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ ም ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቁ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ፡፡ ከንቲባው በዛሬው እለት በከተማዋ በተመረጡ ነባር መንገዶች የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ከልደታ ፀበል እስከ ቡልጋሪያ ማዞሪያ ጋዜቦ አደባባይ እና ከሀይሌ ጋርመንት እስከ ጀሞ አደባባይ እየተገነቡ የሚገኙ 'የታይልስ ንጣፍ' የእግረኛ መንገዶችን ግንባታ ጎብኝተዋል። ከንቲባ ድሪባ እንደተናገሩት፤ ለእግረኞች ጉዞ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ በተመረጡ የከተማዋ ክፍሎች 22 ኪሎ ሜትር የታይልስ ንጣፍ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታ እየተካሄደ ነው። በግንባታው 28 ማህበራት እንደተሳተፉ የገለጹት ከንቲባው የእግረኛ መንገዱ ለእግረኞች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ የከተማዋን ገጽታ እንደሚያሻሽል ተናግረዋል። የእግረኛ መንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ከተማዋ ደረጃውን የጠበቀ የእግረኞች መንገድ ባለቤት እንድትሆን ለማድረግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በቀጣዩ የበጀት አመት በተመሳሳይ 22 ኪሎ ሜትር 'የታይልስ ንጣፍ' የእግረኛ መንገድ ለመገንባት መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ በበጀት አመቱ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ከልደታ ጸበል ቡልጋሪያ ማዞሪያ እስከ ጋዜቦ አደባባይ የሚደርሰው 5 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ 86 በመቶ ደርሷል፡፡ ለግንባታው 550 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበ ሲሆን፤ ግንባታውን አይኤፍኤች ተቋራጭ እያከናወነ ሲሆን፤ ቤስት ኮንሰልታንት ኢንጂነርስ ደግሞ ፕሮጀክቱን ቁጥጥርና ክትትል እያደረገበት ነው፡፡ ከሀይሌ ጋርመንት እስከ ጀሞ አደባባይ 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ከተጀመረ ሶስት ወር የሆነው ሲሆን ግንባታው አስር በመቶ መድረሱ ተገልጿል፡፡ የመንገድ ግንባታው አጠቃላይ ዋጋ 536 ሚሊዮን ሲሆን፤ ሜል ኮንስትራክሽን የተባለ ሀገር በቀል ስራ ተቋራጭ ግንባታውን እያከናወነ መሆኑም ተገልጸዋል፡፡ ዩኒኮን ኮንሰልታንቲንግ የተባለ ሀገር በቀል አማካሪ ድርጅት የግንባታ ሂደቱን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገበት እንደሆነም ታውቋል፡፡ ግንባታውን የወሰን ማስከበሩን ጨምሮ በሀያ አራት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል እንደተገባም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም