ሁለቱን ኮሪያዎች የሚያገናኝ የባቡር መስመር ዝርጋታ ተጀመረ

48

ታህሳስ 18/2011 ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያን የሚያገናኘው የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡

የደቡብ ኮሪያዋን ዋና ከተማ ሴዑልን ከሰሜን ኮሪያዋ ፕዮንግያንግ የሚያገናኘው የባቡር መስመር ዝርጋታ የሰሜን ኮሪያን የባቡር መስመሮች በማሻሻል ከደቡብ ኮሪያ ጋር እንድትገናኝ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ባለፈው ወር የሰሜን ኮሪያን የባቡር መንገድን ለማሻሻል የሚያስችል የጋራ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡

ለባቡር መስመር ዝርጋታው ፕሮጀክት መጀመር የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙንጄ ኢን በሀገራቱ መካከል የቆየውን ውዝግብ ለማርገብ ከተስሟሙባቸው ነጥቦች አንዱ ነው፡፡

የደቡብ ኮሪያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ኪም ሁይን የባቡር መስመር ግንባታው ሁለቱን ሃገራት በአካል ሆነ በመንፈስ በማገናኘት ሀገራቱን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የባቡር መስመር ዝርጋታው አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ በጣለችው ማዕቀብ ምክንያት እክል ሊገጥመው እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የባቡር መስመር ዝርጋታውም ለሁለት ወራት የዘገየው በማዕቀቡ ምክንያት ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የባቡር መስመር ዝርጋታውን በተመለከተ ለሚያጠኑ ሁለት ኮሪያውያን ልዩ ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

አሜሪካ እና አጋሮቿ ግን ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሳሪያ እና የሚሳኤል እንቅስቃሴዋን እስካላቆመች ድረስ ገደቡ ባለበት አድንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡

ምንጭ፡- VOA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም