በሐረና ወረዳ ተፈናቃይ አባወራዎች የመኖሪያ ቤት ችግራችን ተቃሎልናል አሉ

58

ጎባ ታህሳስ 17/2011በባሌ ዞን ሐረና ወረዳ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አባወራዎች የመኖሪያ ቤት ችግራቸው መቃለሉን ገለጹ፡፡

በሌላ በኩል በባሌ ሮቤ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ''በበቂ ሁኔታ ባለመደገፋችን ለችግር ተዳርገናል'' ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ የተፈናቃዮቹን የመጠለያና ተጓዳኝ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረግኩ ነው ብሏል፡፡

በሐረና ወረዳ አስተያየታቸውን ከሰጡ መካከል ወይዘሮ አልፊያ ሱሩር እንደተናገሩት ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ወዲህ ከነልጆቻቸው ጊዜያዊ መጠለያ ስር ከቆዩበት ሁኔታ ወጥተው መንግሥትና የአካባቢው ማህበረሰብ የመኖሪያ ቤት ጥያቄያቸው በመመለሱ ተደስቼያለሁ ብለዋል፡፡

ሌላው የወረዳው ተፈናቃይ አቶ አብዱረህማን ያህያ በበኩላቸው መንግሥት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማስፈር የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥልበት ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በባሌ ሮቤ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በበቂ ሁኔታ ባለመደገፋችን ከልጆቻችን ጋር ለችግር ተዳርገናል ብለዋል፡፡

ከተፈናቃዮቹ መካከል አቶ ጀማል ሐሰን እንዳሉት  የአካባቢው ህዝብ የእህልና የቁሳቁስና ድጋፍ ቢያደርግም፤ እስካሁን የመኖሪያ ቤት ባለማግኘታቸው ከነልጆቻቸው ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረው መንግሥትም ችግራቸውን  እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡ 

ሌላዋ የሮቤ ከተማ ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ መህፉዛ አህመድ በአንድ ሥፍራ አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ አሰልቺ ሕይወትን እየመሩ በመሆናቸው ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጥበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ነዋሪዎች ከተረጂነት ተላቀው ዘላቂ ህይወት የሚመሩበትን ሁኔታ መንግስት እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሐጂ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ተፈናቃዮቹ ከመኖሪያ ቤትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚያነሱት ቅሬታ አግባብነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በሮቤ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች የመኖሪያ ቤት ጥያቄም ሆነ በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት ተፈናቃዮቹ በተለይ ቅሬታ የሚያቀርቡበትን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመፍታት በወረዳዎች የ562 ቤቶች ግንባታ እየተገባደደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም