በሠብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የተያዙ የቀድሞው የመረጃ ደህንነት መስሪያ ቤት ሠራተኞች ጉዳይ ለነገ ተቀጠረ

63

አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሠብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በተያዙ የቀድሞው የመረጃ ደህንነት መስሪያ ቤት ሠራተኞች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ ቀን ለመፍቀድ ቀጠሮ ሰጠ። 

በነ ጎሀ አፅብሀ መዝገብ የተከሰሱት 33 ተጠርጣሪዎች ዛሬ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በተለያዮ ግለሠቦች ላይ የሠብዓዊ መብት ጥሠት በማድረስ፣ በማሠር፣ በማሠቃየት፣ በመደብደብና ወንዶችን በማኮላሸት ተጠርጥረው ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

ፖሊስ በዚህ ወቅት ለፍርድ ቤቱ እንዳቀረበው በተጠርጣሪዎች ላይ መረጃ የማሠብሠብ ስራ እየሠራሁ ነው ብሏል።

በመሆኑም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በሚል የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ የምርመራ ስራውን በሚገባ እያካሔደ ባለመሆኑና በግልፅም በተገቢው መንገድ እያቀረበ ባለመሆኑ የጠየቀው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ መሆን አለበት ሲሉ ተከራክረዋል።           

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም የዛሬው መደበኛ የችሎት የስራ ሰዓት በመጠናቀቁ ውሳኔውን ለመስጠት ለነገ ጠዋት ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም