ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህግ ማሻሻያ ጉባኤ አባላት ምስጋና አቀረቡ

97

አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2011ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፍትህና ዴሞክራሲ ተቋማትን ለማሻሻል እየሰሩ ለሚገኙት የህግ ማሻሻያ ጉባኤ አባላት ምስጋና አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው አባላት ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤የህግ ማሻሻያ ጉባኤ አባላቱ በነፃ አገራዊ ሃላፊነት ወስደው የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎችን ማድረጋቸው "ማገልገል ክቡር መሆኑን" ያሳዩበት በመሆኑ ምስጋና አቅርበውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እውቀትንና ገንዘብ ማጋራት እንዲሁም ነፃ አገልግሎት መስጠት ባህል ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የጉባኤው አባላትም በማሻሻያው ሂደት እስካሁን ያከናወኗቸውን ተግባራት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም የበጎ አድራጎት ማህበራት ህግ ማሻሻያን ማጠናቀቃቸውን ገልፀውላቸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ህግ ማሻሻያው ጥናት ተደርጎ ማርቀቅ የጀመሩ ሲሆን፤ የምርጫ ህጉ ደግሞ በቅርቡ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚላክ የጉባኤው አባላት ገልፀዋል።

የንግድ ህጉንና ሌሎች ህጎችንም የማሻሻል ስራውን በማከናወን ሂደት ላይ መሆናቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የጉባኤው አባላት ለረጅም ጊዜ ሊያገለግል የሚችል ማሻሻያን ታሳቢ አድርገው እንዲሰሩ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የምርጫ ህጉ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተመዝግቦ እንዲንቀሳቀስ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ህጉ የሰዎችን ክብር የማይነካና ግጭት ቀስቃሽ ዘገባዎችን እንዳይሰሩ በህግ ማዕቀፉ እንዲታይ የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የፀረ-ሽብርና የሲቪል ማህበራት ያሉ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች የሕግ የበላይነትን ሳይጋፉ የዜጎችን መብትና ነፃነቶችን እንዲያስከብሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ቀደም ብለው መግለፃቸው የሚያወስ ነው።

የጉባኤው አባላት እያደረጉት ባለው አስተዋፆ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አባላቱ የምስክር ወረቀት የሚያገኙበት የምስጋና መድረክ እንደሚዘጋጅላቸው ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከ4 ወራት በፊት በዐቃቤ ሕግ የተዋቀረውን የሕግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ አባላት የሕግ ማሻሻያዎችን በመከለስና ምክረ ሃሳብ በመስጠት ላደረጉት የነፃ አገልግሎት የጉባዔውን አባላት ማመስገናቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም