የቤጉህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ጉባዔ ነገ ይካሄዳል

57

አሶሳ ታህሳስ 17/2011የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ጉባኤውን ነገ ሊያካሂድ ነው፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አበራ ባዬታ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ማዕከላዊ ኮሚቴው በሚያደርገው ጉባዔ የፓርቲው ሊቀመንበር የመልቀቂያ ጥያቄ መርምሮ ውሳኔ መስጠት ዋነኛ አጀንዳው ይሆናል፡፡

ለፓርቲው ተተኪ ሊቀመንበር መምረጥና በተጓደሉ ሥራ አስፈጻሚዎች አባላት ምትክ ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል፡፡

''ድርጅቱን እስከ ማፍረስ የደረሱ የስትራቴጂክ አመራር እጦት ችግሮች በፓርቲው ውስጥ መኖራቸው ተደርሶበታል” ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፡፡

በቅርቡ በተደረገው የፓርቲው መደበኛ ስብሰባ ጸረ-ዴሞክራሲያዊነትና ቡድንተኝነት እንደታየ የተናገሩት አቶ አበራ ፣ ችግሮቹን ለማረም ከኢህአዴግ ጽህፈት ቤትጋር በመሆን አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅቱን ለአንድ ዓመት ያህል በሊቀመንበርነት መምራታቸውን የተናገሩት አቶ አበራ ፣ ፓርቲው  ቡድንተኝነት፣የሥልጣን ሸኩቻና የፓርቲው አደረጃጀት ችግሮች እንደሚታዩበት ገልጸዋል፡፡

የሥራ መልቀቂያ ያቀረቡት ችግሮቹ  ባለመቃለላቸው እንደሆነም ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው የመልቀቂያ ጥያቄውን ተቀብሎ ተግባራዊ ካደረገ ፤ ኅብረተሰቡን በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አቶ አበራ አረጋግጠዋል፡፡

ቤጉህዴፓ የክልሉን ብሄረሰቦች ባማከለ መልኩ በ2002 የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት ሲሆን፣ማዕከላዊ ኮሚቴው 59 አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም