የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ የመማር ማስተማር ስራውን ጀመረ

63

ባህርዳር ታህሳስ 17/2011 በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ተስተጓጉሎ የነበረው የመማር ማስተማር ስራ መጀመሩን  ዩኒቨርስቲው  አስታወቀ።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት  ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት የተቋሙ የጥበቃ ሰራተኛ በተኮሰው ጥይት የአንድ ተማሪን ህይወት ማለፉና ሌላ አንድ ተማሪ በመቁሰሉ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ነበር።

በዚህም  ምክንያት ባለፉት ሰኞና ማክሰኞ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ተስተጓጉሎ መቆየቱን  አስታውሰው ፤ ተማሪዎችን በማወያየት ማረጋጋት መቻሉን አስረድተዋል።

የዩኒቨርስቲው የአመራር አካላትና የተማሪዎች አደረጃጀቶችን በመጠቀምም በአምስቱም ካምፓሶች መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ ዛሬ መጀመሩን ዶክተር አነጋግረኝ አስታውቀዋል።

የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶችም ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲማሩ በመምከር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

"በቀጣይም የመማር ማስተማር ስራው ያለምንም እንከን እንዲከናወን ከተማሪዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራትና ለሚያነሷቸውን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።

የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ያሬድ አለባቸው በበኩሉ በተቋሙ የተፈጠረው አጋጣሚ ሁሉንም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ያሳዘነና ያልተጠበቀ ድርጊት እንደነበር ገልጿል።

በድርጊቱ ቁጭት የፈጠሩ ተማሪዎች ጉዳዩን በመቃወም ለሁለት ቀናት የመደበኛ የመማር ማስተማር ስራውን መስተጓጎሉን አመልክቶ ፤ ችግሩን በበሰለ መንገድ በመነጋገር ወደ ሰለማዊ ሁኔታ መመለስ መቻሉን ተናግሯል።

"የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሃገራዊም ሆነ ቤተሰባዊ ድርብ ኃላፊነት አለባቸው"  ያለው ተማሪ ያሬድ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰከነና በተረጋጋ መንገድ በመወያየት እልባት መስጠት እንደሚገባም  አሳስቧል።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ለሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል የሰላም ዩኒቨርስቲ እንዲሆንም የሚነሱ  ጥያቄዎች ከበላይ አመራሩ ጋር በመነጋገር ፈጥነው እንዲፈቱ ህብረቱ እየሰራ መሆኑን የህብረቱ ፕሬዚዳንት ገልጿል፡፡

በተማሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው ግለሰብ ፖሊስ በተጠርጣሪነት በቁጥጥር  ስራ በማዋል  ጉዳዩን እያጣራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም