በከተማዋ የአገልግሎት እርካታ ለማምጣት እርምጃ ቢወሰድም አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ተገለጸ

70

አዳማ ታህሳስ 17/2011 በየደረጃው በሚገኘው የመስተዳደሩ መዋቅሮች የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ የአገልግሎት እርካታን ለማምጣት የማስተካከያ እርምጃ ቢወሰድም አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡

ከ1ሺህ 400 በላይ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደሩ  ሴክተር መስሪያ ቤቶች  የተሳተፉበት የግማሽ በጀት ዓመት ግምገማዊ መድረክ በአዳማ አባ ገዳ አዳራሽ ዛሬ ተጀምሯል።

በመድረኩ የከተማው አስተዳደር ተወካይ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ እንዳሉት አስተዳደሩ አዲስ ሪፎርም  ጀምሯል ፤ ይህም ከህዝቡ በእለት ተዕለት የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስና የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታ ለማምጣት ነው፡፡

ከተጀመረው ሀገራዊ ለውጡ ጋር ሪፎርሙን ለማሳካት ባለፉት ስድስት ወራት ፈፃሚውንና አስፈፃሚውን በአስተሳሰብ ፣ በአመለካከት፣በአቅም ማብቃትና ማዘጋጀት ተጀምሮ ተስፋ የሰጡ እርምጃዎች መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለረዥም ዓመታት በኢንቨስትመንት ስም  ተይዘው  ሳይለሙ የተቀመጡ መሬቶች የማስመለስ፣የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ማሻሻል፣ ህገ ወጥ ንግድን በመከላከልና ወደ ህጋዊ መረብ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ መሰረተ ልማቶች ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ፣በከተማዋ  ህገ ወጥነትን ከማስወገድ አንፃር አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም "በየደረጃው የሚገኘው የአስተዳደሩ መዋቅሮች አሁንም በሚፈለገው መልኩ የህዝቡን ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ላይ ወጥነት የላቸውም "ብለዋል።

ዜጎች የሚፈልጉትን አገልግሎት በወቅቱና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲያገኙ ማድረግ በየደረጃው ከሚገኘው አመራርና ፈፃሚዎች የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑንም ተናግረዋል።

"አሁንም ከብልሹ አሰራር የፀዳ የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ላይ ክፍተት አለብን" ያሉት አቶ ተስፋዬ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና በከተማዋ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እውን በማድረግ ለህዝቡ የተገባው ቃል ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የግምገማዊ መድረኩ ዓላማ በከተማዋ የተጀመረውን የሪፎርም ሥራዎችን ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ከማስኬድ አንፃር ባለፉት ስድስት ወራት በየሴክተርሩ የተከናወኑትን ተግባራት፣ ድክመቶችና ጠንከራ ጎኖችን በመለየት የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነ አመልክተዋል።

አቶ ተስፋዬ ብልሹ አሰራር፣የሀብት ብክነት፣ሙስናና የተደራጀ ዝርፊያ በማስወገድ ከተማዋ በሙሉ አቅም ሪፎርም ውስጥ እንድትገባ  ለማስቻል እንደሆነም አብራርተዋል።

አስተዳደሩ ባዘጋጀው በዚሁ የአራት ቀናት መድረክ  ከአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የተወጣጡ የየሴክተሩ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም