ቤተክርስቲያኗ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና የሕዝቡን አንድነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች

58
ጋምቤላ ታህሳስ 17/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና የሕዝቡን አንድነት ለማጠናከር እንደምትሰራ አስታወቀች፡፡ ቤተክርስቲያኗ አገራዊ አንድነትን አስመልክታ  ያስተላለፈችውን ውሳኔ ተከትሎ ለጋምቤላ ክልል የሃይማኖት አባቶች ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋምቤላ፣የደቡብ ሱዳን፤የቤንሻንጉልና የምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኗ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና የሕዝቡን አንድነት ለማጠናከር  ጥረት እያደረገች ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶችን ለመፍታትና በሕዝቡ መካከል የነበረውን የአንድነት መንፈስ ለመመለስ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አቡነ ሩፋኤል አሳስበዋል፡፡ በተለይም የሃይማኖት አባቶች የአገር አንድነትን በመስበክ የሕዝቡ አብሮነት ስሜት ለመመለስ  ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጠይቀዋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ጸሐፊ ቀሲስ በላይ ጸጋዬ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዋ በተጨማሪ አንድነትን በመስበክ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ቤተክርስቲያኗ ዜጎች በኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለምንም የዘርና የቀለም ልዩነት በጋራ ለአገሪቱ እድገት እንዲሰሩ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ  ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች መካከል የሚስተዋሉ የተለያዩ ግጭቶች ቤተክርስቲያኗን እንዳሳሰባት ነው የገለጹት፡፡ በመሆኑም የሕዝቡን አንድነትን በማጠናከርና ሰላም ለማረጋገጥ ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ቀሲስ መላከኃይሌ  ምህረት በሰጡት አስተያየት ቤተክርስቲያን ሁሌም አንድነትን በመስበክ በዜጎች መካከል አብሮነት እንዲጠናከር ድርሻዋን በመወጣት ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፤ አገራዊ አንድነትን ለማምጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡ አባቶቻችን አንድነቷን ጠብቀው ያስተላለፏትን አገር ለቀጣዩ ትወልድ አንድነቷ እንደተጠበቀ ማስተላለፍ አለብን ያሉት ደግሞ ሌላው የስልጠናው ተካፋይ መላከጸሐይ አባ ገብረማርያም ናቸው፡፡ በመሆኑም አገራዊ አንድነትን ለመጠበቅና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም  ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እያጋጠሙ ያሉትን የሰላምና የጸጥታ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ከሚፈጥራቸው መድረኮች በተጨማሪ   የእምነት ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም