ሚኒስቴሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየውን የበጀት አጠቃቀም ችግር ሊያሻሽል አልቻለም

129
አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2011 የትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያለውን ከፍተኛ የበጀት አጠቃቀም ችግር ሊያሻሽል አለመቻሉ ተገለጸ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኦዲት ግኝት መፍትሔ ትግበራ ለመምራት ከተቋቋመው ጊዜያዊ የቅንጅት ኮሚቴ ጋር ውይይት አካሂዷል። በምክር ቤቱ የተቋቋመው ኮሚቴ ለስድስት ወራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኦዲት ግኝት ላይ ቁጥጥርና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱ ተመልክቷል። በወቅቱ ይፋ እንደተደረገው ቀደም ብሎ በተካሄደው የኦዲት ግኝቶች በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የገንዘብ ጉድለቶች ተስተውለው ነበር። ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንዳሉት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኦዲት በተረጋገጡ ግኝቶች ለመንግስት ገቢ መሆን ያለበትን ሃብት ተመላሽ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ክፍተቶች ታይተዋል። ከዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ጋር ተያይዞ ያሉ የካሳ ክፍያና አግባብ ያልሆኑ ወጪዎች መፍትሄ የሚሹ በመሆናቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሊያስተካክል ይገባል ነው ያሉት። በግዥ ምክንያት ለሚፈጠሩ ምዝበራዎች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት የሚሰራው የገንዘብ ሚኒስቴር በማዕቀፍ የሚገዙ እቃዎች ወቅታዊ መሆናቸውን ማጤን እንደሚኖርበትም አሳስበዋል። ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለታ ስዩም የሕግ አግባብን በመከተል የተመዘበረን የህዝብና የመንግስት ገንዘብ ለማስመለስ በተደረገው ምርመራ ከ170 ተቋማት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ተመዝብሯል ብለዋል። ከነዚህ ውስጥ በ20 ዩኒቨርስቲዎች የገንዘብ ብክነቱ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አስረድተዋል። የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ የተቋማቱን ችግሮች እስከ ጥር 30 ቀን 2011 ድረስ እንዲፈታና ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር። ይሁን እንጂ ማስተካከያዎችን ተፈጻሚ ማድረግ አለመቻሉንና በቀጣይም የአሰራር ስርዓቱን በማሻሻል ያልተፈቱ ችግሮች ማቃለል እንደሚገባው ነው የጠቆሙት። ዩኒቨርሲቲዎች መመሪያዎችን እየጣሱና ሃብትን እያባከኑ መሆኑን በኦዲት ግኝት ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት አፈ-ጉባኤው በዋናነትም ለግንባታ፣ ለትምህርት ግብአትና የተማሪዎች የምግብ ወጪ ከመመሪያው ውጪ እንዲፈፀም ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። በቀጣይም ኮሚቴውን በቁጥርም በብቃትም እንዲጨምር በማድረግ እስከ ጥር 30 ሚኒስቴሩ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ይደረጋል ብለዋል። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በሰጡት ምላሽም "የኦዲት ግኝቱን እንዲከታተል ምክር ቤቱ በአዲስ መልክ ያቋቋመው ኮሚቴ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ አጭር በመሆኑ ችግሩን በወቅቱ ለመፍታት አልተቻለም፣ ለዚህም ተጨማሪ ግዜ ይሰጠን’’ ብለዋል። ሚኒስቴሩ ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኦዲት ግኝቶችን እንዲያስተካክል የተሰጠውን ማሻሻያ በመቀበል ያሻሻላቸው ስራዎች እንዳሉ በመጠቆም። ሰኔ 2010 ዓም የኦዲት ግኝት መፍትሔ ትግበራን ለመምራት የተቋቋመው ጊዜያዊ የቅንጅት ኮሚቴ ከትምህርትና ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር የተውጣጡ አባላትን ይዟል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም