የትራፊክ አደጋ የበርካቶችን ህልም እያጨናገፈ ነው

64
አዲስ አበባ  ታህሳስ 16/2011  በትግራይ ክልል ሽሬ እንደስላሴ ተወልዳ ያደገችው የ26 አመቷ ወጣት አምለሱ የውብሸት ከስድስት አመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ በከባድ ተሽከርካሪ አደጋ እንደረሰባት ትናገራለች። ወጣቷ በደረሰባት አደጋ ሳቢያም እግሮቿ ከጥቅም ውጭ በመሆናቸው የመቆረጥ እጣ ገጠማቸው። ይህም በመሆኑ የግል ስራ እየሰራች ስትማር ከነበረችበት የ3ኛ ዓመት የኮሌጅ ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገዳለች። በአሁኑ ወቅትም ድጋፍ የሚያደርግላት ሰው ባለመኖሩ ራሷን ለማስተዳደርና ትምህርቷን ለመቀጠል መቸገሯን ትናገራለች። የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ማሪቱ ሲሳይ ደግሞ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ አንድ እግራቸው እንዲቆረጥና አንድ አይናቸው እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። በደረሰባቸው አደጋ ሳቢያ ሙሉ ለሙሉ የሰው እጅ ላይ መውደቃቸውንም ይናገራሉ። ወይዘሮዋ የልጆቻቸው አባት ህይወት በማለፉ በጽዳት ስራና ድንች ጠብሰው በመሸጥ ልጆቻቸውን ያሳደጉ እንደነበር አስታውሰው ከአደጋው በኋላ ግን ሶሰት ልጆቻቸውን ጨምሮ  በሰዎች እርዳታ ኑሯቸውን እየገፉ ይገኛሉ። በተመሳሳይ አደጋ  ከስምንት አመታት በፊት ታላቅ ወንድማቸውን ያጡት አቶ መስፍን ኢያሱ በበኩላቸው የወንድማቸው ሞት ቤተሰባቸው ላይ ያስከተለውን ሀዘንና ጫና በምሬትና ፀፀት ይናገራሉ። የትራፊክ አደጋ የበርካቶችን ህልም እያጨናገፈ በመሆኑ ሁላችንም ተረባርበን የመፍትሄው አካል ልንሆን ይገባል በማለትም ሃሳባቸውን ቋጭተዋል። በ2010 ዓ.ም ብቻ በትራፊክ አደጋ 5 ሺህ 180 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 3 ሺህ 36 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ  በየዕለቱ በአማካይ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በአራት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንደሚደርስ ከአዲስ አበባ የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኤጀንሲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ11ኛ ጊዜ “መንገዶች ታሪክ አላቸው” በሚል መሪ ቃል አለም አቀፍ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ መርሃ ግብር  በአዲስ አበባ አካሂዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች፣የተጎጂ ቤተሰቦችና ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተው ስለ ትራፊክ አደጋ አስከፊነትና አደጋውን ለመቀነስ መከናወን የሚገባቸውን ስራዎች ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅሬኛ ሄርጳ  ኤጀንሲው የትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስኤዎችን በመለየት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። የትራፊክ ፍሰትና የተሽከርካሪዎች ፍጥነት መቆጣጠሪያ መሰረተ ልማቶችን መገንባት፣ጠጥቶ ማሽከርከርን መቆጣጠር፣ የግንዛቤ ስራዎች ማከናወንና ሌሎች ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል። ሆኖም የትራፊክ አደጋን በመቀነሱ ረገድ ለውጥ አምጥተናል ብለን በድፍረት መናገር አይቻልም ብለዋል። የመርሃ ግብሩ አላማም ዜጎች የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡና የትራፊክ አደጋ መቀነስ ላይ ንቅናቄ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም