በርካታ የቤት ስራ የሚጠይቀው የአጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ

84
አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011  ኢትዮጵያ በዓለምና አህጉር አቀፍ መድረክ በአስመዘገበችው የአትሌቲክስ ውጤትና ታሪክ ስሟ ጎልቶ ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ይታወቃል። በአትሌቲክሱ እንድትጠራ ያደረጓት የውድድር ዘርፎች የረጅም ርቀቶች ሲሆኑ፤ እነርሱም የ5 ሺ እና የ10 ሺ ሜትር ውደድሮች ናቸው። ነገር ግን በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በእርምጃና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ኢትዮጵያ በዓለምም ሆነ አህጉር አቀፍ መድረክ ከተወሰኑ አጋጣሚዎች ውጪ ውጤታማ አይደለችም። በአሁኑ ወቅት በነዚህ የውድድር ዓይነቶች ብቁ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራትና ውጤታማ ለመሆን እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ዛሬ ዓመታዊው የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጀመር ሶስት የፍጻሜ ውድድሮችና 14 የማጣሪያ መካሄዳቸውን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በውደድሩም በ3 ሺ ሜትር መሰናክል ሴቶች መስዋዕት አስማረ ከሃዋሳ ከተማ አሸናፊ ስትሆን፤ ሎሚ ሙለታ ከቡራዩ ከተማ ብዙዋየሁ መሐመድ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በሴቶች ርዝመት ዝላይ አርአያት ዲቦ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ መሆን የቻለች ሲሆን፤ አሉንካን ደሞጋ ከሲዳማ ቡናና  ሌላኛዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወዳዳሪ ኪሩ ኡማን ሁለተኛና ሶሰተኛ ደረጃን ይዘዋል። በወንዶች ዲስከስ ውርወራ የሲዳማ ቡናው ለማ ከተማ አንደኛ ሲወጣ የመከላከያው ሃይሌ ወረደ ሁለተኛ ገበየሁ ገብረየሱስ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል። በውድድሮቹ ላይ በተወዳዳሪዎች ላይ በአሰለጣጠን፣ በልምምድና ቴክኒክ ስራዎች ላይ ጉድለት እንዳለ ተስተውሏል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመከላከያ ስፖርት ክለብ የዝላይ አሰልጣኝ ሻምበል ኡጉላ ኡባንግ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በውድድር አይነቶቹ ላይ ከሌሎች አገሮች ጋር ለመፎካከር የሚያስችል አቅም አላት። ሆኖም እስከአሁን ለውድድሮቹ በቂ ትኩረት አልተሰጣቸውም። ለውድድርና ልምድ የሚያስፈልጉ የስፖርት ቁሳቁሶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላት፣ በዓመት ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ማነስ እንዲሁም የአሰልጣኝና የተወዳዳሪዎችን አቅም የሚያጎለብቱ ተከታታይ ስልጠናዎች አለመስጠት የውደድር ዓይነቶቹ እንዳያድጉ ማድረጉን ነው ያመለከቱት። በሌሎች ጎረቤት አገሮች በአጭር፣ መካከለኛ፣ የሜዳ ተግባራትና የእርምጃ ተወዳዳሪ እምቅ ችሎታ ያላቸውን አትሌቶች ብቃታቸውን እንዲያድግ ለማድረግ ወደ ውጭ ልከው እንደሚያሰለጥኑ የጠቆሙት ሻምበል ኡጉላ፤ በኢትዮጵያ ግን ይህ ነገር እምብዛም እንደማይታይ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በውድድር ዓይነቶቹ በተክለ ሰውነትና በጉልበት ጥሩ አቅም ያላቸው አትሌቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ዋነኛው ጉዳይ አትሌቶቹ የሚጎላቸውን የቴክኒክ ችግር ሳይንሳዊ በሆነ ስልጠና መሙላት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። በውድድሮቹ ላይ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ ኢትዮጵያ ውጤታማ ልትሆን የማትችለበት ምክንያት እንደሌለ ነው ሻምበል ኡጉላ ያስረዱት። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፤ ሻምፒዮናው አጭር፣ መካከለኛ፣ የሜዳ ተግባራትና የእርምጃ ተወዳዳሪ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ሻምፒዮናው በውድድር ዓይነቶቹ ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን የሚፈትሹበትና የአቋም መለኪያ ውድድር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል። በውድድር አይነቶቹ ኢትዮጵያ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተሳትፎ ማድረጓን ጠቁመው፤ የሚመዘገበው ውጤት ከሌሎች አገሮች አኳያ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ያሳያል። በሐምሌ 2010 ዓ.ም ናይጄሪያ አሳባ ከተማ በተካሄደው 21ኛው የአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች ከ100 ሜትር ጀምሮ መሳተፏን አውስተው፤ የተገኘው ውጤት መሰረታዊ ችግሮች እንዲለዩ አጋጣሚ እንደፈጠረ አመልክተዋል። በውድድር አይነቶቹ ውጤታማ ለመሆን በአሰለጣጠን፣ በልምምድና ቴክኒክ ስራዎች በመለወጥ ጊዜው ከደረሰበት ሁኔታ አኳያ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። በአሰለጣጠን በኩል ያለውን ክፈትት ለመሙላት በጋና፣ ኩባና ደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገሮች ከሚገኙ አሰልጣኞች ጋር በመነጋገር በኢትዮጵያ መጥተው እንዲያሰለጥኑ ጥረት አሰልጣኞቹ ያላቸው አቅም ያን ያህል አመርቂ እንዳልሆነ አንስተዋል። ከውጭ የሚመጡት አሰልጣኞች ከኢትዮጵያውያኖቹ መሻል እንዳለባቸው አንስተው ያለው ነገር ያለውን ጥረት በመቀጠል የተሻሉ አሰልጣኞች እስኪገኙ ድረስ ለኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች አቅማቸውን ማጎልበት የሚችሉበት ተከታታይ ስልጠና ለመስጠት በእቅድ መያዙን ተናግረዋል። አሰልጣኞቹንም ውጭ አገር በመውሰድ ልምድ እንዲቀስሙ የማድረግና ታዋቂ አሰልጣኞች በኢትዮጵያ መጥተው ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ እንደሚደረገም ነው አቶ ቢልልኝ ያስረዱት። የውድድር አማራጮችን ማስፋት፣የስፖርቱን ቁሳቁሶች ማሟላትና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ነው የገለጹት። በአጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ውድድሮች እድገት ክለቦች፣አሰልጣኞችና ተወዳዳሪዎች የየበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ዛሬ በተካሄደው ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ በተጨማሪም በቅደም ተከተል የሁለት ሺ፣ የ1 ሺ 500 እና የአንድ ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በነገው የሻምፒዮና የሁለተኛ ቀን ውሎ ሰባት የፍጻሜና በሁለቱም ጾታዎች የ100 እና የ400 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። ከክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች ከሚገኙ 25 ክለቦች የተወጣጡ 706 አትሌቶች በሻምፒዮናው ላይ የሚተሳተፉ ሲሆን ለተወዳዳሪዎች በድምሩ ከ200 ሺህ ብር ላይ ሽልማት ተዘጋጅቷል። የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል። መከላከያ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም