የአማራና የትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች በሜዳቸው ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

68
አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2011 ህዳር 9 ቀን 2010 ዓ.ም አዲግራት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ፋሲል ከተማ እንዲሁም ወልድያ ላይ ወልድያ ከተማና ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት  ጨዋታቸውን ማድረጋቸው ይታወቃል። በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ፋሲል ከተማ መካከል ጨዋታው እየደረገ ባለበት ሰዓት እንዲሁም ወልድያ ከተማና ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጨዋታው ሳይጀመር በፊት በደጋፊዎች ረብሻ መነሳቱ አይዘነጋም። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአማራና የትግራይ ክልል ክለቦች በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ በመወሰን በ2010 ዓ.ም የነበሩ የሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም መደረጋቸው ይታወሳል። ክለቦቹና በገለልተኛ ሜዳ በመጫወታቸው በሜዳቸው ሊያገኙት የሚችሉትን ጥቅም ስላሳጣቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ቅሬታ አቅርበዋል። ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደው  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራር ጉዳዩን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ሲገልጽ ቆይቷል። በተያዘው የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ባህርዳር ላይ ባህርዳር ከተማ ከስሁል ሽረ እንዲሁም በአምስተኛ ሳምንት መቐለ ላይ መቐለ ሰባ እንደርታ ከባህርዳር ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል። ለዚህም በምክንያትነት የተነሳው የትግራይና የአማራ ክልል እግር ኳስ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ አይካሄዱም የሚል ነበር። ታህሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተደረገው ስብስባ የትግራይና አማራ ክልል ክለቦች የእርስ በርስ ጨዋታዎቻቸውን በየሜዳቸው ለማድረግ ተስማምተው ነበር። በስብሰባ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳ፣ የሁለቱ ክልሎች ክለብ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችና የጸጥታ አካላት ተገኝተውበትም ነበር። ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረው የነበሩት የባሕር ዳር ከተማ እና ስሑል ሽረ፣ የፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም የመቐለ ሰብዓ እንደርታ እና ባሕር ዳር ከተማ በባለሜዳዎቹ ከተማ እንዲካሄድ መስማማታቸው ይታወቃል። በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት፣በአፍሪካ አህጉራዊ የክለብ ውድድሮችና ሌሎች ምክንያቶች የተራዘሙ ተስተካካይ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። ነገ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከስሑል ሽረ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከፋሲል ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት እንዲጫወቱ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው ነበር። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሁንም ተስተካካይ ጨዋታውን በድጋሚ ያራዘመ ሲሆን ያረዘመበትን ምክንያትም በግልጽ አላሳወቀም። ክለቦቹና ክልሎቹ እንደተስማሙ ቢገለጽም የጨዋታው በድጋሚ መራዘም ጉዳዩ መፍትሔ እንዳላገኘ የሚያመላክት ነው። የሁለቱም ክልሉ ክለቦች ከአንድ ዓመት በላይ እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ጨዋታ በሜዳቸው ማድረግ  አልቻሉም። በሌላ በኩል ፌዴሬሽኑ ነገ ከቀኑ 11 ሰአት በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9:00 ላይ ሊያደርጉ የነበረውንም ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሟል። ሌሎች ተስተካካይ ጨዋታዎች ግን በወጣላቸው መርሃ ግብር እንደሚያካሄዱ አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በሜዳ እድሳት ምክንያት በሐረር ስታዲየም ጨዋታውን ሲያደርግ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ  የስታዲየም እድሳት አብዛኛው ስራ በማጠናቀቁ ነገ በድሬዳዋ ስታዲየም ከደቡብ ፖሊስ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ያከናውናል። ሐሙስ ታህሳስ 18 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባጅፋር ከቀኑ 11 ሰአት ላይ ይጫወታሉ። በሌላ በኩል በስምንተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ታህሳስ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በጅማ ስታዲየም ጅማ አባጅፋር ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ታህሳስ 22 ቀን 2011 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲዘዋወር ተደርጓል። ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በወጣላቸው መርሃ ግብር ማካሄድ ፈተና የሆነበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ምክንያቶች ጨዋታዎች ማራዘሙ ከክለቦች በኩል ቅሬታ እያስነሳበት ይገኛል። የመርሃ ግብሮች መቆራረጥና በወጣላቸው መርሃ ግብር አለመካሄድ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ገጽታ ሆኗል። እስካሁን በተደረጉ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የደረጃ ሰንጠረዡን ሃዋሳ ከተማ በ14 ነጥብ ሲመራ፣ፋሲል ከተማ ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ 11 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ስሑል ሽረ፣ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ አግቢነት የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ 5 ጎሎች ሲመራ፣ የሀዋሳ ከተማዎቹ ታፈሰ ሰለሞንና እስራኤል እሸቱ በተመሳሳይ 4 ጎሎች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው በሶስት ግቦች ይከተላሉ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም