በአካባቢ ጸጥታ ማስከበር ለተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ድጋፍ ተደረገ

72
ማይጨው ታህሳስ 16/2011 በጸጥታ ማስከበር ስራ ለተሰማሩ የመኾኒ ከተማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ድጋፍ የሚውል ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን  በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ አዘቦ ወረዳ አስተዳዳር ገለፀ። የገንዘብ ድጋፍ የተደረገው ወጣቶቹ የጀመሩትን በጎ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማበረታታት ነው፡፡ የወረዳው አስተዳዳር የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ግርማይ  ከላሊ የገንዘብ ድጋፍ በተለይ ወጣቶቹ እንቅስቃሴያቸው ላይ ለሚያጋጥማቸው የእለት ተእለት የስራ ማስኬጃ የሚያውሉት መሆኑን አስረድተዋል። በመኾኒ ከተማ ባለፈው እሁድ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም  የተሰባሰበው ይሄው ገንዘብ ከወረዳው የመንግስት ሰራተኞችና ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከተሰበሰበው የድጋፍ ገንዘብ ውስጥ 326 ሺህ ጥሬ ገንዘብ በመኾኒ ከተማ ከሚኖሩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ሲሆን ቀሪው የመንግስት ሰራተኞች ከወርሃዊ ደሞዛቸው ካዋጡት የተገኘ ነው ተብሏል፡፡ በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ከተሳተፉት መካከል የመይዳ ራያ ሆቴል ባለቤት ዲያቆን ሞገስ ንጉሰ በሰጡት አስተያየት፣"ያለወጣቶች ተሳትፎ የአካባቢ ዘላቂ ሰላም መጠበቅ አይቻልም"ብለዋል። ወጣቶቹ የከተማዋን ሰላም በማረጋገጥ ባከናወኑት ተግባር በመደሰታቸው የ10 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። በተጨማሪም ለአንድ ዓመት የሚቆይና በየወሩ የአንድ ሺህ ብር ድጋፍ ለመስጠትም ወስነዋል፡፡ ወጣቶቹ  በፀጥታ ማስከበር ስራ በመሰማራታቸው ህዝብ በሰላም ወጥቶ  እንዲገባ በማስቻሉ የአምስት ሺህ ብር ድጋፍ መስጠታቸውን የተናገሩት ደግሞ በመኾኒ ከተማ  የትንሳኤ ሆቴል ባለቤት ወይዘሮ ብርሃን ኪዳነ ናቸው። የወጣቶቹ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲጠናከር ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም በየወሩ  የአንድ ሺህ ብር ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል። በፕሮግራሙ ማብቂያ ወቅት የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም እንደተናገሩት፣  ወጣቶቹ በራሳቸው ተነሳሽነት የጀመሩት የፀጥታ ማስከበር ስራ ለሌሎች ምሳሌ ነው። ሆኖም  ወጣቶቹ የህዝቡን ሰላም ሲጠብቁ በኑሯቸው መጎዳት እንደሌለባቸው ጠቅሰው  "ለወጣቶቹ ዘላቂ የገቢ ምንጭ የሚሆን  የስራ ዕድል መፍጠር ትኩረት ይሰጠዋል"ብለዋል። ወጣቶቹ በፀጥታ ማስከበር ስራ በመንቀሳቀስ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ይዘው በሚንቀሳቀሱና በህብረተሰቡ ሰላም ላይ ስጋት በሚፈጥሩ ግለሰቦች ላይ  ባደረጉት ቁጥጥር ውጤት ማምጣታቸውም ተመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም